Search

የ26 ዓመቷ እናት በአንድ ጊዜ አራት ሕፃናትን በሰላም ተገላገለች

ሰኞ ነሐሴ 04, 2018 251

በጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል 26 ዓመት ወጣት እናት በአንድ ጊዜ አራት ልጆችዋን በሰላም መገላገሏን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት እናትየዋ እና አራቱ ልጆቿ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደገሚኙ ተገልጿል።

የሕክምና ሂደቱን በበላይነት የሰጡት እና የመሩት የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር የሆኑት እሸቱ ታደለ እና ሌሎች የሆስፒታሉ የሕክምና ቡድን ቀዶ ሕክምናውን በስኬት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ዶክተር እሸቱ ስለ ሕክምናው ዝርዝር ሁኔታ ሲያብራሩ፣ አራት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ በሰላም ማገላገል በሆስፒታሉ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ገልጸው ከሦስት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ አንዲት 24 ዓመት ወጣት እናት በሪፈር ከጤና ጣብያ ወደሆስፒታሉ ገብታ አራት ሕፃናትን በሆስፒታሉ በሰላም መገላገሏን አስታውሰዋል።

የአሁኑን ለየት የሚያደርገው 26 ዓመቷ እናት አራት ፅንስ መፀነስዋን በሆስፒታላችን ክትትል በምታደርግበት ወቅት በመታወቁ ለእናቲቱ እና ለሚወለዱት ጨቅላዎች ደኅንነት ከፍተኛ የሆነ ክትትል እንደሚያስፈልግ ከግምት ውስጥ በማስገባት የወሊድ ቀኗ ከመድረሱ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በዋርድ በማስተኛት ሌት ከቀን ክትትል እንደተደረገላት ተናግረዋል።

በመውለጃ ቀኗም በጨቅላ ሕፃናት ክፍል ለሕፃናቱ ማረፍያ እና አጋዥ ማሽኖች ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሆስፒታሉ ተገልጋይ ተኮር አሠራርን ስለሚከተል በከፍተኛ የሕክምና ቴክኖሎጂ እና መሳሪያዎች የተደራጀ በመሆኑ፣ በየዘርፉ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ወጣት እና ቁርጠኛ የሕክምና ባለሙያዎች ስብስብ በመኖሩ አገልግሎቱ በቁርጠኝነት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ለእናቶች እና ሕፃናት የተሰጠ ትኩረት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር እሸቱ እንደ አሁኑ አይነት አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ እርግዝናዎች በሚከሰቱበት ጊዜ "እናት ጤና፤ ልጅም ደህና" የሚለውን ሀገራዊ የጤና መርሕ በተግባር ለማዋል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር እደሆነም ዋና ስራአስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ማብራራታቸውን ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: