Search

ወደ ከፍታ የሚያሻግሩን ሦስቱ ምሰሶዎች፡- የኢትዮጵያ የቀጣይ አምስት ዓመታት የብልጽግና አቅጣጫዎች

ማክሰኞ ነሐሴ 05, 2018 99

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገትና ዘላቂ ኅልውና ለመወሰን የሚያስችሉ ሦስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርገዋል።

እነሱም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር ናቸው። እነዚህ ሦስት አምዶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካ ቅርፅ የሚወስኑ መሠረታዊ ማዕቀፎች ናቸው።

በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጦች እና በዓለም አቀፍ የምግብ ገበያ ፍላጎት መጨመር ምክንያት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የኅልውና ጉዳይ ሆኗል። ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል ማድረግ የእርዳታ ጥገኝነትን የሚያስቀር እና ብሔራዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመደመር መንግሥት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገራችንን ከውጭ ሀገር ስንዴ ገዢነት ወደ ላኪነት አሸጋግሯታል።

በመጪዎቹ ዓመታት ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ሰብሎች በማስፋት፣ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን፣ ሜካናይዜሽንን እና የአፈር ለምነት ማሻሻያዎችን በመጠቀም ሙሉ በሙሉ በምግብ ራስን መቻል ትልቁ ግብ ነው።

የሀገር እድገት ያለ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶች አይታሰብም። ባለፉት ዓመታት የተጀመሩት ሀገራዊና ቀጣናዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው ለኢኮኖሚው ትልቅ ማነቃቂያ ይሆናል።

በዚሁም በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ እና የተጀመረውን የዳንጎቴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎችን ማጠናቀቅ፣ እንዲሁም የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተጀመሩ የቤቶች ግንባታ ሥራዎችን ማስፋፋትና ማጠናቀቅ ቀዳሚው ሥራ ይሆናል።

የከተሞች ውበት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያጎለብቱ የኮሪደር ልማት፣ የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ የሀገራችንን የኢኮኖሚ አቅም በእጥፍ ያሳድገዋል።

ምንም ያህል የምግብ ዋስትና ቢረጋገጥ እና መሰረተ ልማት ቢገነባ፣ ጠንካራና ተቋማዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ከሌለ እድገቱ ዘላቂ ሊሆን አይችልም።

በመሆኑም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው። የፍርድ ቤቶች፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የፀጥታ ተቋማት ገለልተኝነትና አቅም በማሳደግ፣ በሀገራችን ባሉ መሠረታዊ ልዩነቶች ላይ በውይይትና በምክክር መፍትሔ በመፈለግ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሌላኛው ትልቅ ኃላፊነት ነው።

እነዚህ ሦስት ምሰሶዎች እርስ በእርስ የተሳሰሩ ሲሆኑ፣ የምግብ ዋስትና የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ሲያሟላ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ሞተር ይሆናሉ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ደግሞ የእነዚህ ሁሉ ስኬቶች መጠለያ የሚሆን አስተማማኝና ሰላማዊ ሀገር ይፈጥራል።

የመጪዎቹ 5 ዓመታት ጉዞ እነዚህን እቅዶች ከወረቀት ወደ መሬት በመቀየር ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግናዋ የምታደርገውን ጉዞ በማፋጠን ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: