Search

የመኪና ማቆሚያን ለሌላ አገልግሎት ሲጠቀሙ የተገኙ የህንፃ ባለቤቶች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

ሓሙስ ነሐሴ 08, 2017 227

የመኪና ማቆሚያን ለሌላ አገልግሎት ሲጠቀሙ የተገኙ  የህንፃ ባለቤቶች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለፀ፡፡

በባለስልጣኑ የፓርኪንግ እና የመንገድ ትራፊክ መሰረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በመዲናዋ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚሄዱ ተገልጋዮች ተሽከርካሪያቸውን ከዋና መንገድ ዳር ስለሚያቆሙ ነው ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ መጨናነቅን ለማቃለል ባለፈው ዓመት የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ደንብ ቁጥር 165/2016 ማፅደቁንም ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግም በ11ዱ ክፍለ ከተሞች የህንፃ ስር የመኪና ማቆሚያን ለተለያዩ አገልግሎት ሲጠቀሙ የነበሩ 1 ሺህ 286 ህንፃዎችን በመለየት ስፍራውን ለተፈቀደለት ዓላማ እንዲያውሉ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ዳር የሚገኙ በጥናት የተለዩ 1 ሺህ 227 ህንፃዎች ስር ያሉ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በመለየት መንገድ ላይ ይቆሙና ከተማውን ያጨናንቁ የነበሩ ከ 21 ሺህ 600 በላይ ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙበት ማድረግ ተችሏል ብለዋል አቶ ቢኒያም፡፡

የህንፃ ስር የተሽከርካሪ ማቆሚያውን አሁንም ለፑል ቤት፣ ለስቶር፣ ለጭፈራ ቤት፣ ለጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ለሌላ አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉ 55 የህንፃ ባለቤቶች መቀጣታቸውንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በየተመኙሽ  አያሌው

#ebc #ebcdotstream #AddisAbaba #Parking

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: