Search

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአጭር ጊዜ የሙያ ስልጠናዎችን መስጠት ሊጀምር ነው

ሓሙስ ነሐሴ 08, 2017 170

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የአጭር ጊዜ የሙያ ስልጠናዎችን መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሴኔት የአጭር ጊዜ የፕሮፌሽናል ሰርቲፊኬት መርኃ ግብሮችን ለመተግበር የሚያስችል ማዕቀፍ ማፅደቁን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል፡፡

ሴኔቱ ያፀደቀው የአጭር ጊዜ የፕሮፌሽናል ሰርቲፊኬት መርኃ ግብር የሰራተኞችን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

ማዕቀፉ በሚታወቅ ደረጃ ተምረው የተመረቁ ሙያተኞች በስራ ላይ ሆነው የሙያ  ክህሎታቸውን ለማስፋት እና ለማሳደግ ከሳምንታት እስከ ወራት የሚሰጥ ሙያዊ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡

እንደዚህ አይነት የአጭር ጊዜ የፕሮፌሽናል ስልጠናዎች በፍጥነት ለሚለዋወጠው ገበያ ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ እና ሙያተኞች የእድሜ ልክ ተማሪ የሚሆኑበትን ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የሚሰጠው በተለመደው የትምህርት ስርዓት አሰጣጥ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎች፣ የሙያ ማህበራት ወይንም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ላይ በጀማሪ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ ለሙያተኞቻቸው የሚሆን የሙያ ሰርተፍኬት ሲፈልጉ የሚሰጥ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ሰራተኞች የሚያጋጥማቸውን የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት  ለመሙላት እና ለማሳደግ የሚረዳ ሲሆን እንደ የደረጃው ከሳምንታት እስከ ወራት የሚሰጥ ይሆናልም ብለዋል፡፡

ሁሉም የፕሮፌሽናል ሰርቲፊኬት መርኃ ግብሮች የጥራት ደረጃዎችን የሚያሟሉ እና ከሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

ማዕቀፉ በተደራጀ ቅርፅ ለባለሙያዎች፣ ለኢንዱስትሪዎች እና ለሙያ ማህበራት ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ችግር ፈቺ የሥልጠና ፕሮግራሞችን ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

በሐይማኖት ከበደ

#ebc #ebcdotstream #AddisAbabaUniversity #Professionalprograms

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: