ረጅም ዓመታት ትኩረት ተነፍጓቸው የቆዩት የአዲስ አበባ ወንዞች እና የወንዝ ዳርቻዎች፣ ዛሬ ላይ የከተማዋን ገጽታ እና የነዋሪዎቿን ሕይወት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ የልማት ማዕከላት እየሆኑ መጥተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት የተመረቀው እና 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ በመዲናዋ የሥነ ምኅዳር እና የከተማ አስተዳደር ታሪክ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስልታዊ እርምጃ ነው።
ከዚህ ቀደም የከተማዋ ወንዝ ዳርቻዎች ለጎርፍ አደጋ፣ ለቆሻሻ መጣያነት እና ለደኅንነት ስጋት የተጋለጡ ነበሩ። የእንጦጦ-ቀበና ፕሮጀክት ግን ይህንን በመቀየር፣ አካባቢውን ወደ ውድ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ሀብትነት ለውጦታል።
በተለይም ዘመናዊ ድልድዮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች መገንባታቸው አካባቢውን ለኢንቨስትመንት፣ ለአነስተኛ የንግድ ዕድሎች እና ለከተማ ቱሪዝም ምቹ በማድረግ የወንዝ ዳርቻዎችን የሀገር ውስጥ ገቢ ማስገኛ ማዕከል ያደርጋቸዋል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ በአዳጊ ሀገራት ከተሞች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመከላከል ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ መፍትሔዎች ወሳኝ ናቸው።
በዚህም ረገድ ፕሮጀክቱ ያካተታቸው የወንዝ መከላከያ ግንቦች እና ሰፊ የአረንጓዴ መሸፈኛዎች ከተማዋን ከጎርፍ አደጋ ከመታደግ ባለፈ፣ የከተማ ሙቀትን በመቀነስ እና አየርን በማጽዳት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
ይህ ተግባር አዲስ አበባ የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ከከተማ ፕላን ጋር በተግባር ያቆራኘ ሥራ ነው። የፕሮጀክቱ መሳካትም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን የአደራ ትሥሥር በተግባር ያሳየ ሆኗል።
ውስብስብ የከተማ ማደስ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት ማጠናቀቅ መቻል፣ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም ማደጉንም ያረጋግጣል። ይህም የዜጎችን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል እና በመዲናዋ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተገባውን ቃል በተጨባጭ መሬት ላይ ያወረደ የልማት ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል።
በሔዋን ጌታቸው