ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን ዕድገት ከተበታተኑ አሠራሮች ወጥታ የተቀናጀ የኢኮኖሚ መሠረት እንድትጥል እያስቻላት ይገኛል።
የቴሌኮም ዘርፉን በማዘመን እና ለገበያ ክፍት በማድረግ የተጀመረው ይህ ጉዞ ሀገራችንን ወደ ላቀ የዲጂታል ዘመን እያሸጋገራት ነው።
የመሠረተ ልማት እና የክፍያ ሥርዓት አብዮት
በቅርብ ዓመታት የቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር ከ37.9 ሚሊዮን ወደ 85 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ለሀገራዊው የዲጂታል ትሥሥር እና ለገበያ ተሳትፎ የማይናወጥ መሠረት ጥሏል።
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መስፋፋት ደግሞ ሌላው ታሪካዊ ስኬት ነው። ከዚህ ቀደም በውል የማይታወቀው ዓመታዊ የዲጂታል ግብይት መጠን አሁን ላይ ወደ 24.2 ትሪሊዮን የኢትዮጵያ ብር ከፍ ብሏል።
ይህ ግዙፍ አሃዝ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን ግብይት በመቀነስ ግልጽነትን የፈጠረ ሲሆን፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ግልጽ የሆነ እና የታለመ የፋይናንስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ምቹ ሥርዓት ፈጥሯል።
አካታችነትን ያረጋገጠው ዲጂታል መታወቂያ
የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማሳደግ በኩል ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከባዶ ተነሥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ46.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመዝገብ ቸሏል።
ፋይዳ በገበያ የሚጠየቀውን የምዝገባ እና የማረጋገጫ ወጪዎችን በእጅጉ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
አስተማማኝ የማንነት ማረጋገጫ በመስጠትም የፋይናንስ አካታችነትን ይበልጥ እውን እያደረገ ነው።
ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም እና የወደፊቱ ራዕይ
በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት ታቅዶ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሳካው የ"5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ ያረጋገጠ ነው።
ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ 5 ሚሊዮን 5 ሺህ 146 ሰልጣኞች ተመዝግበዋል።
ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
ይህ በዲጂታሉ ዓለም የተጀመረው ታሪካዊ ምዕራፍ የጉዞው ማብቂያ ሳይሆን ብሔራዊ ራዕይን ይበልጥ ማፋጠኛ መነሻ ነው።
በመሆኑም እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ አዲስ ግብ ተሰንቋል።
በተለይም ወጣት ተማሪዎች የክረምቱን ወቅት በዋዛ ከማሳለፍ ይልቅ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጠውን ይህንን ሥልጠና በመውሰድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው የዲጂታል መሪዎች እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
እነዚህ ሁሉ እመርታዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ፉክክር ውስጥ ተወዳዳሪ ብቻ ሳትሆን መሪም እንድትሆን የሚያደርጓት ጽኑ መሠረቶች ናቸው።
በለሚ ታደሰ