ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ የተከናወነው የወንዞች ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ውበት ከማልበስ ባለፈ የነዋሪዎቿን የደኅንነት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የቀየረ ትልቅ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ነው።
ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት የወንዞችን የተፈጥሮ ማንነት ከመገንባት ጀምሮ ሰፊ የሕዝብ መጠቀሚያዎችን በማካተት የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ ቀይሮታል።
ቀደም ሲል ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች የሚጣሉባቸው በክረምት ለጎርፍ አደጋና ለከባድ ጠረን ተጋላጭ የነበሩ የከተማዋ ክፍሎች፤ ዛሬ ወደ ንጹሕ፣ ጤናማና እፎይታን ወደሚሰጡ አረንጓዴ ስፍራዎች ተለውጠዋል።
ይህ የልማት ሥራ የአካባቢ ሥነምህዳርን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የኅብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ የትውልድ ታላቅ ዐሻራ ነው። ለዚህ ለውጥ አስደናቂ ማሳያ ከእንጦጦ ተራራ ስር ተነስቶ እስከ ቀበና ድልድይ የተዘረጋው የልማት ፕሮጀክት ነው።
በአጠቃላይ ሰፊ ቦታን የሸፈነው ይህ ፕሮጀክት፣ ትናንት ማለፍ የሚያስጠላ የነበረውን ስፍራ ወደ ሕዝብ መዝናኛና የኢኮኖሚ ምንጭነት ቀይሮታል። በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራት ተፈጥሮን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በልዩ ጥበብ ያስተሳሰሩ ናቸው።
ለተፋሰስ ጥበቃና ለውሃ መጠን መጨመር የባሕር ዛፎች ተመንጥረው በሀገር በቀል እፅዋት መተካታቸው፣ የእርከንና የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች የአፈር መሸርሸርን ሙሉ በሙሉ አስቁመዋል። በዚህም ምክንያት ትናንት በቆሻሻ የተሞላው ወንዝ ዛሬ ኩልል ባለ ውሃ መፍሰስ ጀምሯል፤ አካባቢውም ለብዝኃ ሕይወት መመለሻና ለሰላም ቀጣናነት በቅቷል።
ይህ ፕሮጀክት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል በተቀናጀ መሠረተ ልማት በመገንባቱ፣ የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስርና እረፍት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
በወንዙ ዳርቻ የተገነቡት የእግረኛ መንገዶችና የኮንክሪት ወለሎች ነዋሪዎች ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀሱና እንዲገናኙ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል። ማዶና ማዶን የሚያገናኙት ተንጠልጣይና የተለያዩ ድልድዮች የከተማዋን ትስስር ከማሳለጥ ባለፈ የቱሪስት መስኅብ ሆነዋል።
ከእንጦጦ ጀምሮ የተዘረጋው የሃይኪንግ መንገድ አወቃቀርም ስፖርታዊና ጤናማ የኑሮ ዘይቤን ያበረታታል። በተጨማሪም ማታ ላይ ልዩ ውበት የሚሰጡ የመንገድ መብራቶች፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ የልጆች መጫወቻዎች እና ቤተ መጻሕፍት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የዚህ ፕሮጀክት ሌላው ትልቅ አንድምታ የከተማ ግብርናን፣ የምግብ ዋስትናንና የኢኮኖሚ እድሎችን አቀናጅቶ የያዘ መሆኑ ነው።
በልማቱ የተተከሉ በርካታ ዛፎች ለውበት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እንጆሪ፣ ማንጎ እና አፕል ያሉ የፍራፍሬ ምርቶች የሚገኙባቸው ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመረው ዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራም የከተማዋን የወንዝ ዳርቻዎች ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚቻል ያሳየ ስልታዊ ስኬት ነው።
እንዲሁም የጽዳት ንቅናቄውን በዘመናዊ ዲጂታል አሰራር (QR ኮድ) መምራት መጀመሩ የልማቱ የዘመናዊነት መገለጫ ነው።
በአጠቃላይ ትናንት ከፍተኛ የደኅንነትና የጤና ስጋት የነበሩ ቦታዎች ዛሬ ወደ ሕዝብ መጋቢነት፣ ወደ ሥራ ዕድል ፈጠራና ወደ ዓይን ማረፊያነት ተለውጠዋል።
ይህ ፈጣንና ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ በኢኮኖሚ ንቁ እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተዋሃደች ዘመናዊ መዲና በማድረግ፣ የወደፊቷን ዕጣ ፈንታ በጽኑ መሠረት ላይ ጥሎታል።
በበረከት ሽመልስ