በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ጋር የማጠቃለያ ውይይት አካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የበጀት አመዳደብ ዕቅዱ የራስን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፣ 80 በመቶውን በጀት ከገቢ ለመሰብሰብ የታሰበ ብቻ ሳይሆን የኢትጵያን 10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ መሰረት ያደረገ የበጀት ድልድል እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከ4 በመቶው በላይ የነበረውን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዕዳ መጠን ወደ 1.4 በመቶ ዘቅ ማድረግ እንደተቻለ እና 30 በመቶ የተያዘው በጀትም ይህንን ዕዳ ለመክፈል የሚውል መሆኑን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ አስፈላጊ የሆኑት ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ መንገድ እና የከተማ ልማት ከፍተኛው በጀት ከተያዘላቸው ዘርፎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) ለመጭው ትውልድ ከዕዳ ነፃ ሀገር ለማስረከብ ሲባል መንግሥት ከተያዘው በጀት ውስጥ 500 ቢሊየን ብሩን የዕዳ ክፍያ ጫናን ለመቀነስ መያዙ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላነሧቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ ቁጠባን መሠረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶች ጥያቄ የሌለበት አካባቢ የለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከአሁን በፊት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ብቻ እስከ 2 ትሪሊየን ብር እንደሚያስፈልግና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚያስፈልጉትን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጀት ጋር በተያያዘ በቀጣይ በጥናት እንደሚመለስ ጠቁመዋል።
በህይወት አበበ