የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንጦጦ - ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ከንቲባዋ የእንጦጦ - ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት በስኬት እንዲህ ባማረ መልኩ ለማጠናቀቅ፤ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ደማቅ ዐሻራ እንድናኖር አብራችሁን የሰራችሁ የመሰረተ ልማት ተቋሞቻችን አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ ኮንትራክተሮች፥ አማካሪዎች፣ የቀን ሰራተኞች፣ ባለሙያዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ታላቅ አክብሮትና ምስጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ያለማቋረጥ እንደዚህ ያሉ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሰርተን ለትውልድ ስጦታ አድርገን ስናቀርብ በከተማችን በጀት እንጂ በብድር ወይም በእርዳታ አይደለም።
በመሆኑም የከተማችን ግብር ከፋዮች፣ የገቢ ሰብሳቢና የፋይናንስ ተቋሞቻችን አንድ ላይ ተደምረን በትብብር ያሳካነው ልማት በመሆኑ ሁላችሁንም በከተማችን ነዋሪዎች፣ በአስተዳደራችን እና በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ነው ያሉት።
ለከተማዋ ነዋሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባዋ፣ ይህንን እጅግ ውብና ማራኪ የመዝናኛና ጤና መጠበቂያ ሆኖ የተጠናቀቀ የቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት በዋናነት የተሰራው ለእናንተ ነውና መጥታችሁ እንድትጎበኙ፣ እንድትዝናኑ እጋብዛችኋለሁ ብለዋል።
ልማቱም በዘላቂነት ለትውልድ እንዲተላለፍ እንዲያንከባክቡና እየጠበቁ እንዲጠቀሙበት የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።