Search

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የ70 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

ሰኞ ሰኔ 22, 2018 71

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን 70 ሚሊዮን ዩሮ የረጅም ጊዜ የብድር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተተገበረው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም እና የልማት ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይህ የልማት አጋርነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ አለው።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሽግግር ለማገዝ በተለይም በኃይል፣ በግብርና እንዲሁም በውሃ ዘርፎች የተጀመሩ መዋቅራዊ ሪፎርሞችን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው 70 ሚሊዮን ዩሮ የረጅም ጊዜ ቀላል የብድር ስምምነት፣ የተጀመረውን የሪፎርም ጉዞ እና የልማት ሥራዎችን በቀጥታ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እና የዲፕሎማሲ ጥረት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ጣሊያን የምታደርገው ድጋፍ በቀጥታ ከሚሰጠው የገንዘብ እገዛ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማግኘት የሚገባትን ድጋፍ እንድታገኝ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ አስተዋጽዖ ማበርከቷንም አንስተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ፣ ይህ ድጋፍ የሪፎርም ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያግዝም ተገልጿል።

ስምምነቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ የሪፎርም ጉዞ ላይ ያላትን ፅኑ እምነትና ዘላቂ አጋርነት በድጋሚ ያረጋገጠ መሆኑም ተመልክቷል።

በሂሩት እምቢአለ