Search

የወደፊቷ ኢትዮጵያ - በቱሪዝም ልማት የሚገነባ የብልጽግና ተስፋ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 57

 

 (የዕለቱ መልዕክት)

ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማህደር በመሆኗ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በፈጠራ እና በልማት ክህሎት የቱሪዝም ተስፋዋን እንደ አዲስ እያበሰረች ያለች ሀገር ናት።

በታሪክ አድማስ ውስጥ የነበረው የቱሪዝም ዘርፋችን ዛሬ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሞተርነት ተሸጋግሯል። ይህ ለውጥ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ነባሩን የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብት በዘመናዊ ዕይታ እና በቁርጠኝነት የመቅረጽ ውጤት ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠችው ትኩረት የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ኢትዮጵያዊነትን ለዓለም የምናስተዋውቅበት የገጽታ ግንባታ መንገድ ሆኗል።

የቱሪዝም ልማታችን የጀርባ አጥንት የሆኑት መሠረተ ልማቶች እና መዳረሻዎች፣ የስትራቴጂያችን ማዕከል ናቸው። ከሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተከናወኑት ሥራዎች የነበሩን የተፈጥሮ ጸጋዎች ከማልማት ባለፈ ለወደፊት ትውልድ ተረካቢ የሚሆኑ የብልጽግና ተምሳሌቶች ናቸው።

የኮሪደር ልማት ሥራዎችም ከተሞቻችንን ለቱሪስቶች ምቹ እና ማራኪ ከማድረጋቸው በላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ረጅም ዘመን የፈተኑ የመሠረተ ልማት ችግሮችን እየፈቱ ይገኛሉ።

ቱሪስት በቆየ ቁጥር ለኢኮኖሚያችን የሚጠቅም መሆኑን በመረዳት የሆቴል እና የመስተንግዶ አገልግሎቶችን በጥራት እና በዘመናዊነት ማሳደግ፣ ከዚህ በኋላ ምርጫ ሳይሆን የግዴታ ተግባር ሊሆን ይገባል።

ሆኖም ትልቅ የቱሪዝም ሀብት መያዝ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ሀብቱን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የገበያ ልማት ሥራዎች ወሳኝ ናቸው። ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ የምናደርገው ማስተዋወቂያ፣ ካለን የዲጂታል አቅም ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ስም በዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ በጥብቅ ማስቀመጥ ይኖርበታል።

ይህ ሁሉ ጥረት ግን የሠለጠነ የሰው ኃይል ከሌለው ውጤታማ አይሆንም። በዘርፉ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ቀጣይነት ያለው ሥልጠና መስጠት፣ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ እና የአገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርጉ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

 

የቱሪዝም ልማት የሁሉንም ዘርፎች ትሥሥር የሚጠይቅ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነው። በአንድ በኩል ልማትን ስናከናውን በሌላ በኩል ደግሞ ያለንን ቅርስ እና ተፈጥሮ ጥበቃ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል።

የተፈጥሮ እና የታሪካዊ ስፍራዎች ዘላቂነት ተጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የጋራ ኃላፊነታችን ነው። የቱሪዝም ትንሣኤያችን የአንድ ወገን ሳይሆን የዜጎች ሁሉ የጋራ ጥረት ውጤት ነው።

እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆን ይህን ታላቅ የልማት ፍሰት በዓለም አደባባይ ማስተጋባት ይኖርበታል።

ኢትዮጵያን የዓለም ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ የምናደርገው ጉዞ በቁርጠኝነት እና በተባበረ ክንድ ከቀጠለ አሁን ካለንበት ከፍታ በላይ እንደምንሻገር እርግጠኞች ነን።

የቱሪዝም ዕድገት የብልጽግናችን ማረጋገጫ  የትንሣኤያችን መገለጫ ነው።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል