Search

ተስፋን እንትከል፤ መጻዒውን ጊዜ እንገንባ፡- የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 45

የለውጡ መንግሥት አዲስ የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤን ወደ ሥራ በማስገባት፣ ስጋት ላይ ወድቆ የነበረው የኢትዮጵያ አረንጓዴነት እንዲያገግም እና የደን ሽፋን እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

መርሐ ግብሩ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ማኅበረሰቡ ለችግኝ ተከላ ያለው አመለካከት ከመሠረቱ የተቀየረ ሲሆን የነበረውን የሥራ ባህልም እየተለወጠ መጥቷል ብሏል።

በየዓመቱ ችግኝ በሚተከልበት በዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ ማኅበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት እየተሳተፈ መሆኑ፣ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገልጿል።

እንደ ቢሮዉ መልዕክት ከትንሽ እስከ ትልቅ በተለመደው የችግኝ ተከላ እና በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በግለሰብም ሆነ በቡድን አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ የችግኞቹ መጽደቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ ተደርጓል።

ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጉዞ ዋስትና እየሆነ መጥቷል ብሏል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በዚህ ጉዞ ከ 28 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች መተከላቸውን የቢሮው መረጃ ያመላከተ ሲሆን ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ፣ የተጎዱ መሬቶችን መልሶ በማገገም እና ደንን በማልማት ረገድ በተሠራው ሥራ ትልቅ ድል መመዝገቡ ተጠቅሷል።

በተደረገው ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ እና ጥበቃ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ 85 በመቶ በላይ የጸደቁ ሲሆን የኦሮሚያ ደንም በቀደመው እሴትና ሥርዓት እየተመራ በሁሉም አቅጣጫ በተሠራው ሥራ ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 29 በመቶ ማደግ ችሏል ብሏል ቢሮዉ።

በዚህ ዓመትም በአንድ ጀንበር እና በተለመደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለተለያዩ ጠቀሜታዎች የሚውሉ 5.3 ቢሊዮን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።

በዚህ ጉዞ ዜጎች የነገውን ጥላ ዛሬ ላይ በመገንባት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ድልን ለማረጋገጥ እና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ተስፋቸውን መትከላቸው ወሳኝ መሆኑን የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስገንዝቧል።