Search

ድብቁን ሚስጥር የገለጠው ስኬታማው ተልዕኮ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 56

አባቶች ሲተርቱ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ይላሉ። ሀብት፣ ብልጽግና እና ዕድል እሩቅ ሳይሆኑ  በገዛ እጃችን መዳፍና በቤታችን ደጃፍ እያሉ ፣ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ መኖራችንን ስንመለከት፣ የውኃ ሀብታችን ለሌሎች የቱሪዝም ሀብት ሲሆን ወንዞቻችን ለሌሎች ሃገራት የቱሪዝም መስህብ ሲሆኑ ስንመለከት፣ የዝሆን ጥርስና ሌሎች የእንስሳት ሃብቶቻችን ሌሎችን ከበርቴ ሲያደርጉ ስንመለከት በእርግጥም ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ሲቆረጥ መኖሩን ለማሳየት ከዚህ በላይ ህያው ምስክር የለም።

ኢትዮጵያ እጅግ የላቀ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የባህል ማዕድ የታደለች ምድር ብትሆንም፣ ለዘመናት ግን በድህነት ስንማቅቅ መኖራችን አሳዛኝ የታሪክ ተቃርኖ ነበር። የተፈጥሮ ውበትና የታሪክ ድንቆች ሞልተው በተረፉባት ሀገር፣ ህዝቦቿ ግን የኋላቀርነትና የችግር መገለጫ ሆነው መቆየታቸው ትልቅ ምጸት ነበር።

ይህ የሆነው አቅም አጥተን ሳይሆን፣ ያለንን የክብር ማዕዘን በአግባቡ የሚለይ፣ የሚያይና የሚያለማ ብቁ እይታና አመራር ስላጣን፣ እንዲሁም በገዛ ሀብታችን ላይ የበይ ተመልካች ሆነን በመቆየታችን ምክንያት የመጣ ፈተና ነበር።

ይህንን የታሪክ መጋረጃ የቀደደው፣ የብዙዎቻችንን ዐይኖች የገለጠውና አዲስ ብሩህ ተስፋ የሰነቀው የመደመር ፍልስፍና ነው። መደመር ቱሪዝምን እንደ ተራ የመዝናኛ ዘርፍ ወይም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ስራ አድርጎ አይመለከተውም። ይልቁንም የሀገርን ገጽታ በአዲስ መልክ የሚገነባ፣ ሕዝባዊ ኩራትንና ብሔራዊ አንድነትን የሚያድስ፣ እንዲሁም የሕዝብን ሕይወት በፍጥነት የሚቀይር ታላቅ ድብቅ አቅም አድርጎ ይተረጉመዋል።

የመደመር መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ፣ ይህንን ጥልቅ እውቀት ወደ ተጨባጭ ሀብትነት ለመቀየር ቱሪዝምን ከአምስቱ መሰረታዊ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሞተሮች (Pillars) አንዱ አድርጎ በፖሊሲ ደረጃ በቁርጠኝነት በመቅረጽ ወደ ተግባር ገብቷል።

ይህ ትክክለኛ ፖሊሲ ለዘመናት ተዘንግቶና ተደብቆ የኖረውን የተፈጥሮና የባህል ጸጋ ወደሚጎበኝ፣ ወደሚሸጥ፣ የስራ ዕድል ወደሚፈጥርና ሀገራዊ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ወደሚያመነጭ ህያው የኢኮኖሚ ምንጭነት አሸጋግሮታል።

በስትራቴጂና በትግበራ ደረጃ የመጣው ይሄው የለውጥ ጉዞ ደግሞ ዛሬ ከመሬት በላይ የሚታይ እውነተኛ ተዓምር ሆኗል። የመደመር መንግሥት በወሰደው ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ልዩ የትግበራ ፍልስፍና፣ ድቅድቅ ጨለማና የተረሱ ስፍራዎች ሁሉ ወደ ብርሃንና ወደ ውበት ማዕከልነት ተቀይረዋል።

ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው ጊዜ በፊት በላቀ የጥራት ደረጃ መጠናቀቃቸው የትግበራ አቅማችንን በጉልህ ያሳያል። ይህ አካሄድ በቱሪዝም ዘርፍም ሙሉ በሙሉ እውን ሆኗል።ለአብነት ያህል፣ ከትናነት ወዲያ በታላቅ ድምቀት የተመረቀው የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን ከዘመናዊ ቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር የአረንጓዴ ልማት ተምሳሌትነቱን በተግባር አሳይቷል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንዲሁም በ“ገበታ ለሀገር” እና በ“ገበታ ለትውልድ” አነሳሽነት የተገነቡት የጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻና ሌሎች በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተፈጥሮአዊ ሀብቶቻችንን ወደ ማይጠፍ የገንዘብና የኢኮኖሚ ምንጭነት የቀየሩ አስደናቂ ማሳያዎች ናቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ የዲጂታል ማስተዋወቅ ስራዎች፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎችና በአዳዲስ ሳቢ በሆኑ መዳረሻዎች ልማት ምክንያት የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ፍሰት እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። በተለይም በከተማ ቱሪዝም፣ በኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) እና በተፈጥሮ መስህቦች አካባቢ የተመዘገበው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የቱሪዝም መናኸሪያ እያደረጋት ይገኛል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በነዚህ አዳዲስ ፓርኮች፣ በዘመናዊ ሆቴሎችና በተያያዥ የአገልግሎት ዘርፎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የስራ ዕድል በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት የተጓዘው ስኬታማ መንገድ ከመደመር እሳቤ የተቀዳ ድንቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው። ሀብታችንን አውቀን፣ አይኖቻችን ተገልጠው፣ በገዛ ደጃፋችን ያለውን ሞፈር መቁረጥ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የበይ ተመልካችነታችንና የድህነት ትረካችን አብቅቷል።

ዛሬ ላይ ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን ጠንካራ የጀርባ አጥንት፣ የሀገራችን አዎንታዊ ገጽታ መገንቢያና የኢትዮጵያ ስም በዓለም አቀፍ መድረክ በክብርና በኩራት ደምቆ የሚነሳበትና ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዋነኛ መድረክ ሆኗል። ይህ ጉዞ በቀጣይም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ብልጽግና የሚያረጋግጥ፣ ትውልድን የሚያኮራና ታሪክን የሚያድስ የማይገታ የለውጥ ማዕበል ሆኖ ወደፊት ይቀጥላል።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ