የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ማጠናቀቂያ ፈተና ከዛሬ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአብረሆት ቤተመጻሕፍት በመገኘት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናው አስጀምረዋል።
ይህ ሀገር አቀፍ ፈተና እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በመላው ኢትዮጵያ በ607 የፈተና ማዕከላት በስድስት ዙር የሚሰጥ ይሆናል።
በዛሬው ዕለትም የመጀመሪያው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የኦንላይን ፈተና መሰጠት የጀመረ ሲሆን ፈተናውን በበይነ መረብ የሚወስዱ ተማሪዎች አስቀድሞ በተዘጋጁ ዙሮች በሲስተሙ ላይ አስፈላጊውን የልምምድ ተግባር ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ለዘንድሮው ብሔራዊ ፈተና በድምሩ 563 ሺህ 501 ተፈታኞች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 306 ሺህ 456ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 257 ሺህ 045ቱ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች መሆናቸው ታውቋል።
ፈተናው በበይነ መረብ እና በወረቀት የሚሰጥ ሲሆን በወረቀት የሚፈተኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 1 እስከ 3 ቀን እንዲሁም የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ፈተናቸውን የሚወስዱ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በኮሌጆች ውስጥ በሚገኙ ማዕከላት እየተሰጠ ነው።