የ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በአብረሆት ቤተመጻሕፍት በመገኘት ያስጀመሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዘንድሮው ዓመት አመርቂ የተማሪዎች ውጤት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ለዚህ ስኬት ይረዳ ዘንድ የተለያዩ ሰፊ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 62 በመቶ ለሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናው በበይነ መረብ በሦስት ዙር እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
ይህ አፈጻጸም አምና ከነበረው የ25 በመቶ የኦንላይን ፈተና አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት ሁሉም ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ መረብ እንዲወስዱ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ይህ የ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከዛሬ ሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በ607 የፈተና ማዕከላት በስድስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የመጀመርያው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና መሰጠት ተጀምሯል።
ለዚህ ፈተና በድምሩ 563 ሺህ 501 ተፈታኞች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 306 ሺህ 456ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 257 ሺህ 045ቱ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች መሆናቸው ታውቋል።
ፈተናው በበይነ መረብ በሦስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በወረቀት የሚፈተኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 1 እስከ 3 ቀን እንዲሁም የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ፈተናቸውን የሚወስዱ ይሆናል።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች በ131 የፈተና ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ ፈተናቸውን በበይነ መረብ እንዲወስዱ የተመቻቸ ሲሆን ይህም የፈተና ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተከናወኑ ዝግጅቶች አካል መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አብራርተዋል።
በብሩክታዊት አስራት