Search

የመደመር መንግሥት፤ የኢትዮጵያን ንጋት አብሳሪ

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 47

ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የቆዩ የፖለቲካ ስብራቶችን በመጠገን፣ የነገዋን ታላቅ ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ላይ የሚገኘው "የመደመር መንግሥት"፣ ከጽንፎች የተላቀቀ ሕብረ-ብሔራዊነትን የተላበሰ፣ የኢትዮጵያን ተደማሪ አቅም እየፈጠረ የሚገኝ እውነተኛ አሰባሳቢ ኃይል ነው።

ይህ መንግሥት ከኢትዮጵያውያን እሳቤና ተሞክሮ በበቀለው የ'መደመር' ፍልስፍና በመመራት፣ ኢትዮጵያን ከነበረችበት ፍጹም የተለየ ወደሆነ ከፍታ እያሻገረ የሚገኝ ተምሳሌት ነው።

የመደመር መንግሥት መሰረታዊ መለያው ከማንኛውም የርዕዮተ ዓለም አምልኮ ነጻ መሆኑ ነው።

እንደ ቀድሞዎቹ የደርግ ወይም የኢህአዴግ ዘመናት፣ ኢትዮጵያን ለውጭ ርዕዮተ ዓለም መፈተሻ ላቦራቶሪ አያደርጋትም። ይልቁንም፣ "ገቢር ነበብነት" በተሰኘው መርህ፣ የትናንትን ስህተቶች በመማሪያነት እየተጠቀመ፣ ዛሬን በትጋት እየገነባ፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ አቅሞችን ሁሉ በመደመር ላይ የተመሰረተ ነው።

የመደመር መንግሥት የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን (Value-Add) የሚያደርግ፣ ልዩነቶችን እንደ ጥንካሬ የሚጠቀም፣ የብሔራዊ አንድነት ምሽግ ሆኖ ኢትዮጵያን ተጋርጦባት ከነበረ የመበተን አደጋ እየታደጋት ነው።

ይህ መንግሥት ከቀደምት ሥርዓቶች የሚለየው "የኢንተርፕረነር መንግሥት" ባህሪው ነው። ፈተናዎችን የሚጋፈጥ ፣ይልቁንም ፈተናዎችን እንደ እድል በመውሰድ፣ ከፈተናዎች ውስጥ መልካም አጋጣሚዎችን የሚያዋልድ፣ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በመገንባት፣ የዜጎችን የመፍጠር አቅም በማነቃቃት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን እያረጋገጠ ነው።

ስንዴን ከውጭ መግዛት አቁሞ ወደ ላኪነት መሸጋገር፣ አረንጓዴ ልማትን በቢሊዮን ችግኞች መተግበር፣ እና የአዲስ አበባን ገጽታ በመቀየር የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የመደመር መንግሥት የተግባር ውጤቶች ናቸው።

የመደመር መንግሥት ራዕይ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያን በሰብዓዊ ልዕልና፣ በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና በአፍሪካዊ ኃይልነት መገንባት ነው። በ2040 በዓለም አርዓያ የምትሆን ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ ሰብዓዊነትን፣ ዲሞክራሲን እና የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ የመግባባት ዴሞክራሲን እየገነባ ይገኛል።

ይህ የመደመር መንግሥት ዜጎችን በብሔር ማንነታቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው መነፅር አይከፋፍልም፤ ይልቁንም በሃሳብ የበላይነት፣ በጋራ ልማት እና በወንድማማችነት እሴት ስር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያሰባስባል።

ባጭሩ፣ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን ለአለም ዕንቁ እና ታላቅ ሀገር እያደረጋት ነው። የድሮውን የመጠፋፋት እና የመሸነናነፍ ፖለቲካ አስቀርቶ፣ "የኢትዮጵያ መደመር" የጋራ አቅም ሆኖ እንዲያብብ በማድረግ ላይ ነው። ይህም አድማስ፣ ኢትዮጵያ እንደ ጥንት ዘመኗ ሁሉ በዓለም መድረክ በክብር የምትሰለፍበት፣ የብልጽግናዋ ጎህ የተቀደደበት ንቃት አብሳሪ ዘመን ነው።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ