በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ሂሳብ አያያዝ ላይ ትኩረቱን ያደረገ እና ለመጀመሪያ ደረጃ የመሬት ሂሳብ መዝገብ ቅድሚያ የሚሰጥ አዲስ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ይህ ፍኖተ ካርታ መሬትን፣ የመሬት አጠቃቀምን፣ ደኖችን እና ተያያዥ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመለካት እና ለመከታተል የሚያስችል የአካባቢ ጥበቃ እና የኢኮኖሚ መረጃዎችን የማቀናጀት ሥራን ያካተተ ነው።
ይፋ በሆነው ሰነድ መሠረት የዕቅዱ ዋና ዓላማዎች የመሬት መራቆትን እና የብዝሃ-ሕይወት መጥፋትን መገምገም፣ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የፖሊሲ እና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን መደገፍ፣ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማትን ማገዝ እንዲሁም የመሬት መልሶ ማቋቋም እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ግንባታ ጥረቶችን መምራት ናቸው።
በተጨማሪም የተፈጥሮ ሀብት ሂሳብ አያያዝ ውኃን፣ ሥነ-ምህዳርንና ካርቦንን እንዲያካትት ለማስፋፋት እና እነዚህን የሂሳብ መዝገቦች በሃገር አቀፍ ዕቅድ እና በበጀት ዝግጅት ውስጥ ለማካተት የሚያስችል መመሪያ በሰነዱ ውስጥ ተካቷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ዲኤታ በረከት ፍሰሀፂሆን እንደገለጹት፤ እነዚህ ሰነዶች ሀገራዊ የጋራ ራዕይን እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም አላቸው።
በተለይም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመቅረጽ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እና ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጋራ ለመስራት ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት መሆኑን ሚኒስቴር ዲኤታው አብራርተዋል።
ይህ የተጀመረው አዲስ አሠራር ኢትዮጵያ ዘላቂ፣ ሁሉን አቀፍ እና ንቁ ልማትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በመድረኩ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት እና የወርልድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በኤዶም አማረ