Search

ፈገግታ እና አክብሮት ለቱሪዝም ስኬት

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 75

የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ዓመታት ባደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቱሪዝምን ከአምስቱ ቁልፍ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ እያለማ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "አንዲት ቪዛ፣ ዓለም በውስጧ!" በሚል መሪ ቃል በተላለፈው ልዩ መሰናዶ ላይ እንዳብራሩት፣ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት በዘላቂነት ሊቀጥል የሚችለው ከመንግሥት ጥረት ባለፈ እያንዳንዱ ዜጋ፣ አገልግሎት ሰጪ እና ባለድርሻ አካል ብሔራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው።

መንግሥት የገነባቸው የተፈጥሮ እና የታሪክ መዳረሻዎች ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ መሠረተ ልማቶቹ ከፍተኛ ጥራት ባለው የአገልግሎት ልህቀት መደገፍ አለባቸው።

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ ማነቆ ሆኖ የቆየውን "ኮስታራነት" "ፈገግታ እና በአክብሮት" መተካት እንደሚገባ ብሔራዊ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ እንግዶች ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡበት የመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ መተግበር ያለበት መሠረታዊ እሴታችን ሊሆን ይገባል።

ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ በመጀመሪያ የሚያጋጥማቸው ማኅበራዊ መስተጋብር በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ አሽከርካሪዎች ጋር ነው።

በመሆኑም እንግዶችን ከአውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎች የሀገራችንን ታላቅ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በተግባር በማንፀባረቅ፣ ፍትሐዊ ዋጋ በማስከፈል እና በታማኝነት በማገልገል የሀገር መልክ ሠሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

እነዚህ አካላት ሀገራችንን በመጀመሪያው ግንኙነት ላይ የሚያስተዋውቁ ብሔራዊ አምባሳደሮች ናቸው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ሆቴሎች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ እንክብካቤዎችን ለእንግዶቻቸው ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ሆቴሎች ጥራት ካለው መስተንግዶ ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ትስስሩን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም ተመላክቷል።

በውጭ ሀገር የሚኖረው የዳያስፖራ ማኅበረሰብም በሀገራችን ላይ የሚሠሩ አሉታዊ እና ገጽታን የሚያጠለሹ ተግባራትን ከማገዝ ተቆጥቦ ትክክለኛዋን እና ውቢቷን ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደራ ብለዋል።

ቀደም ሲል ዳያስፖራው ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጣ ቤተሰቡን ይዞ የሚዝናናበት ጥራት ያለው መዳረሻ የመፈለግ ስጋት ነበረበት።

አሁን ላይ ማራኪ መዳረሻዎች በመገንባታቸው ይህ ስጋት ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል። በመሆኑም ዳያስፖራው ሀብቱን እና ዕውቀቱን ለሀገር ገጽታ ግንባታ እንዲያውል ይጠበቃል።

መላው ዜጋም የተፈጥሮ ጸጋዎችን ከመጠበቅ፣ ፓርኮችን በመንከባከብ እንዲሁም ሰላም እና አንድነትን በማጠናከር የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለሀገር እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግ ሁላችንም በጋራ እንስራ ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) መልዕክት።

በለሚ ታደሰ