የኢትዮጵያ የቱሪዝም እና የቅርስ ልማት ስትራቴጂ ከምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሙ ባሻገር ብሔራዊ ገጽታ የመቀየር፣ የታሪክ ትርክቶችን የመግራትና የባህል ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥልቅ ፖለቲካዊና ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ አለው።
ለዘመናት በውጭው ዓለም ስልታዊ በሆነ መንገድ የተገነባውና ኢትዮጵያን ከረሃብ፣ ከችግርና ከውድቀት ጋር ብቻ አያይዞ የሚያሳየው አሉታዊ ታሪክ፣ ሀገራችን የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌትና ያልተገዛች ብቸኛ ምድር በመሆኗ የተጫነባት የጽንፈኝነት ተጽዕኖ ውጤት ነበር።
ይህንን የጠለሸ ስም ለመቀየርና የሀገራችንን እውነተኛ ታላቅነት ለዓለም ለማሳየት፣ ቅርሶችንና ታሪካዊ ቦታዎችን እንደ ዕዳ ሳይሆን እንደ ብሔራዊ በረከትና ውኅደት መድረክ የመውሰድ አዲስ ምልከታ ተፈጥሯል።
ከዚህ ቀደም ቅርሶች በፖለቲካዊ ክፍፍልና በሰፈርተኝነት ስሜት "የእኔና ያንተ" እየተባሉ አንዱን የማግለል ዝንባሌ ይታይባቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የላሊበላ የህንጻ ጥበብ፣ የሶፍ ዑመር ጥንታዊ ስልጣኔ፣ የፋሲል ግንብ፣ የሀረር ጀጎልና የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫና ኩራት እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ35 በላይ የተዘረፉና የጠፉ ውድ የኢትዮጵያ ቅርሶች፣ የፀሐይ አውሮፕላንንና የዐፄ ቴዎድሮስን ዙፋን ጨምሮ፣ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው የዚሁ የብሔራዊ ማንነትና የታሪክ ተጋድሎ ማሳያ ነው።
ታሪካዊ ቤተመንግሥቶችና የዓድዋ ድል መታሰቢያ መዋቅሮች ትናንት ከነበሩበት የፈራረሰና የተረሳ ገጽታ ወጥተው ዛሬ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የኩራትና የገቢ ምንጭ መሆናቸው መንግሥት የወሰደውን የጥራትና የትክክለኛነት መርህ የሚያረጋግጥ ነው።
በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ የታጀበው ይኸው የቱሪዝም ሥነ ምኅዳር፣ ወጣቶችና ዜጎች በእግር እየተጓዙ ሀገራቸውን እንዲያውቁና እንዲያስተዋውቁ በማነቃቃት፣ ብሔራዊ ተምሳሌቶችን የማብዛትና የመዋሃድ ሰፊ እድል ፈጥሯል።
ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን የመቃወም የቆየ የፖለቲካ ልምምድ ስጋቶችንና ወቀሳዎችን መሰንዘር ቢሞክርም፣ የተሠሩት ሥራዎች ጥራትና የመጡ ለውጦች በተለይ የዲያስፖራዎችና የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ፍሰት ሀገራችን የገነባችውን አዲስ የዲፕሎማሲና የትርክት የበላይነት ያሳያሉ።
በመሆኑም፣ አዲሱ የቱሪዝም ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ታሪክና እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ መልሶ በማልማት፣ ዜጎች ሀገራቸውን ይበልጥ እንዲረዱና እንዲወዱ፣ ዓለምም ስለ ኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንዲቀይር የሚያስገድድ የትርክትና የፖለቲካ ድል ፍሬም ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጥልቅ እውነታ ነው።
በበረከት ሽመልስ