ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የተከተለችውን እና በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን የግብርና መር ኢኮኖሚ መዋቅር በመስበር፣ ቱሪዝምን እንደ አዲስ የኢኮኖሚ ምሰሶ የመቅረጽ ስትራቴጂካዊ ሽግግር ላይ ትገኛለች።
ይህ አካሄድ ዘርፉን ከተለመደው የባህል እና የታሪክ ነጸብራቅነት ባለፈ፣ ፈጣን እና አስተማማኝ የኢንቨስትመንት ትርፍ የሚያስገኝ፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያመነጭና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ቀዳሚ አንቀሳቃሽ ማሽን አድርጎ የመቅረጽ እሳቤ ነዉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚንቀሳቀሰውን የ12.6 ትሪሊየን ዶላር የቱሪዝም ሀብት ለመቋደስ የታለመው ይህ መዋቅራዊ ለውጥ፣ እንደ ማይስ (MICE) ያሉ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚታይባቸውን የስብሰባ፣ የማበረታቻ ጉዞዎች፣ የኮንፈረንስና የኤግዚቢሽን ዘርፎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ያላትን የአፍሪካ የፖለቲካ ዋና ከተማነት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ግዙፍ የአህጉራዊ ትስስር አቅም እንደ መግቢያ በር በመጠቀም፣ የመጡ ዲፕሎማቶችን እና መንገደኞችን በሀገር ውስጥ አቆይቶ የኢኮኖሚ ትራንዛክሽን እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ አዲሱ የምጣኔ ሀብት መነቃቂያ ስልት ሆኗል።
ቱሪዝም በራሱ የቆመ ደሴት ሳይሆን ከኢንዱስትሪ፣ ከአነስተኛ ንግዶች እና ከአገልግሎት ዘርፎች ጋር የተሰናሰለ በመሆኑ፣ አንድ ጎብኝ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የሚበላው፣ የሚለብሰው፣ የሚሸምተውና የሚገለገልበት አጠቃላይ ስነ ምህዳር አብሮ እንዲያድግ ያደርጋል።
ይህንን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ የጎብኝት ሥፍራዎችን ማልማት ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የሰባት አዳዲስ አየር መንገዶች ግንባታ፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ ሪዞርቶች እና ዲጂታል የቦታ ማስያዣ ሠርዓቶች የዘርፉን ማነቆዎች የፈቱ ተጨባጭ እርምጃዎች ናቸው።
የአርባ ምንጭ የኮንፈረንስ ማዕከል እና በሐይቅ ላይ የተገነባው ተንቀሳቃሽ ሬስቶራንት የዚሁ የደረጃና የከፍታ ማሳያ ሲሆኑ ይህ መሰረተ ልማት የግሉን ባለሀብት በከፍተኛ ደረጃ የመሳብ እና የኢንቨስትመንት አቅሙን የማሳደግ ሚና ተጫውቷል።
በሕዝብና መንግሥት አጋርነት፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና በወዳጅ ሀገራት ድጋፍ የለማው ይህ የቱሪዝም ኢኮኖሚ፣ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን በዘንድሮው በጀት ዓመት 1.4 ሚሊየን የውጭ ጎብኝዎችን በመሳብ 5.2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማስገኘት ችሏል።
ከዚህም ይበልጥ የሚያስደምመው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት ሲሆን ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ በመንቀሳቀስ ከ79 ቢሊየን ብር በላይ የኢኮኖሚ ዝውውር መፍጠር ችለዋል።
ይህ በቱሪዝም፣ በኮሪደር ልማት እና በሌሎች መሪ ዘርፎች የተመዘገበው የተቀናጀ ምላሽ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት 10.2 ፐርሰንት የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) እድገት እንድታስመዘግብ ያደረገ ሲሆን ይህም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር አዋጭነት በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው።
በበረከት ሽመልስ