ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር ብትሆንም፣ ለረጅም ዘመናት ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ ብቻ የተደገፈ ነበረ።
በአሁኑ ወቅት ግን፣ ይህንን ምስል ለመቀየር ቱሪዝም እንደ አዲስ የኢኮኖሚ ሞተር እና ዋነኛ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶ ተደርጎ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል።
ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመቀየር የተቀረጹት ስትራቴጂዎችና አዳዲስ መዳረሻዎች የዘርፉን ትንሣኤ እያበሰሩ ነው። ይህንን አዲስ የኢኮኖሚ ሞተር ለማንቀሳቀስ በዋናነት የተከናወነው የመዳረሻዎች ልማትና የመሰረተ-ልማት ግንባታ ነው።
በአዲስ አበባ የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የእንጦጦ እና የአንድነት ፓርኮች እንዲሁም በክልሎች የተገነቡት የ"ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ እና ደንቢ ኢኮ ሎጅ ያሉ መዳረሻዎች የቱሪዝም መልክዓ-ምድርን ቀይረውታል።
በተጨማሪም የክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች መስፋፋትና መዘመን ቱሪስቶች በቀላሉ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ የውስጥ ለውስጥ ትስስርን አጠናክሮታል።
ሌላው የቱሪዝም ትልቁ ፋይዳ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትስስር ነው። ዘርፉ ለወጣቶችና ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረም ይገኛል።
አሁን ላይ ሀገራዊ ትኩረት የተሰጠው ዲጂታላይዜሽን እንደ ‘መሶብ' መተግበሪያ ያሉ የተቀናጁ የዲጂታል አገልግሎቶች የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ቀልጣፋ እያደረገው ነው።
ቱሪስቶች የትራንስፖርት፣ የሆቴል እና የመዳረሻ ትኬቶችን በዲጂታል መንገድ መቁረጥ መቻላቸው ለዘርፉ መነቃቃትና ለጥሬ ገንዘብ አልባ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አጋዥ ሆኗል።
ይህ አዲሱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ከአረንጓዴ ገፅታ ግንባታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እየተከናወነ ያለው መጠነ-ሰፊ የደን ልማትና የብዝኃ ህይወት ጥበቃ የኢኮ-ቱሪዝም አቅማችንን እያሳደገው ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በብሪክስ የአጋርነት መድረክ ያላትን ተሳትፎ እያጠናከረች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ቱሪዝምን ማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደጉም በላይ፣ የኢትዮጵያን አዎንታዊ ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ዋነኛው ዲፕሎማሲያዊ መሳሪያ ነው።
በሔዋን ጌታቸው