ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ አንድ ቪዛ፣ ዓለም በውስጧ” በሚል መሪ ሐሳብ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረክ ከመቀየሩ ባለፈ ከሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተሮች አንዱ በመሆን እየጎላ የመጣውን የቱሪዝም ዘርፍን አስመልክተው ልዩ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
በቃለመጠይቃቸውም፣ ለሁላችንም ትልቅ የቤት ሥራ ሰጥተውናል። በዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ኢትዮጵያን አስውቦ የመሥራት ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም የመግለጥ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ይህ መልዕክት ለአንድ ወገን ወይም ለመንግሥት ተቋማት ብቻ የተሰጠ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በያለበት ሊወጣው የሚገባ ሀገራዊ ጥሪ ነው።
ሀገርን ማስዋብ በአስተሳሰብ፣ በሥራ ባህል፣ በአካባቢ ጥበቃና በልማት ኢትዮጵያን ማደስ ነው። የቱሪዝም አምባሳደር መሆን ደግሞ የሀገራችንን ድንቅ ባህል፣ ታሪክና የተፈጥሮ ጸጋ በምናደርገው እያንዳንዱ የዲጂታል እንቅስቃሴ ለዓለም ማሳየት ነው።
በዚህም በትንሹ ዛሬ በሞባይል ስልክዎ የሚያጋሩት አንድ ቆንጆ የሀገርዎ ምስል፣ የሚያስተዋውቁት አንድ ባህላዊ እሴት ወይም የሚያሳዩት መልካም መስተንግዶ የኢትዮጵያን ገጽታ ይገነባል።
እኛ የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ የቱሪዝም አምባሳደሮች ነን። ስልካችንን፣ እውቀታችንን እና ፍቅራችንን ተጠቅመን ኢትዮጵያን ለዓለም ማስተዋወቅም የውዴታ ግዴታችን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እያንዳንዱ ዜጋ ኢትዮጵያን አስውቦ የመስራት ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም የመግለጥ ኃላፊነት አለበት” ሲሉ ሀገርን ከመገንባት ባለፈ፣ የተገነባውን ውበትና እምቅ አቅም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ የጋራ ኃላፊነት እንዳለብን የሚያሳይም ነው።
ሀገርን ማስዋብ የሚጀምረው ከግል ስብዕና እና ከአካባቢ ጥበቃ ነው ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች የሀገራችንን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ዜጎች በሀገራቸው እንዲኮሩና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲፈጠሩ አድርገዋል።
ዛሬ ዓለም በዲጂታል ትስስር አንድ መንደር ሆናለች። አንድ የውጭ ሀገር ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ቀድሞ የሚመለከተው የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችንን ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በእጁ ላይ ባለው ስማርት ስልክ የሀገሩን መልካም ገጽታ የመገንባት ትልቅ ኃይል አለው።
የታሪክ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ከአክሱምና ላሊበላ እስከ ሶፍ ዑመርና ባሌ ተራሮች፣ ከበለጸጉት አዳዲስ መዳረሻዎች እስከ ባህላዊ መስተንግዶዎቻችን ለዓለም ማስተዋወቅ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋም ኃላፊነት ነው።
ይህንንም ኃላፊነት መወጣት የምንችለው የሀገራችንን ውበትና የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያሳዩ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በምንጠቀማቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች በማጋራት እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ፍቅር በመቀበልና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እገዛ በማድረግም ጨምር ነው።
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሀገር የምታምረው በልጆቿ ጥረት ሲሆን፣ ውበቷ ለዓለም የሚተርፈው ደግሞ በልጆቿ ድምጽ መሆኑንም ያስገነዝበናል።
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትና የተፈጥሮ ዕደ-ጥበብ የሞላባት ሀገር ናት። ይህንን የታደልነውን እምቅ ሀብት አስውቦ የመጠበቅና ለዓለም የማሳየት ኃላፊነታችንን በጋራ የመወጣት ጊዜም አሁን እንደሆነም መገንዘብና መሥራት ይኖርብናል።
በአድማሱ አራጋው