በ2010 ዓ.ም የተከሰተውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያ ጉዞ ፍኖተ ካርታ ሆኖ ያገለግል ዘንድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው "መደመር" መጽሐፍ የቻይንኛ ቋንቋ ትርጉም ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ነው።
መጽሐፉ በቅርቡም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለንባብ እንደሚበቃ ተረጋግጧል።
ባለፉት አሥርት ዓመታት ከአፍሪካ አህጉር ፈልቀው ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ከተሻገሩ ጥቂት አገር በቀል ፍልስፍናዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የሆነው "መደመር" በበርካቶች ዘንድ በትኩረት የሚታይ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል።
መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዓረብኛ እንዲሁም በፓኪስታን የኡርዱ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በቢሊዮኖች የሚነገርለትን የቻይናን የቋንቋ መድረክ በይፋ ለመቀላቀል በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የ"መደመር" መጽሐፍ ወደ ቻይንኛ ቋንቋ መተርጎምና በዓለም ኃያላን ሀገራት ተርታ በምትሰለፈው ቻይና ዘንድ ትኩረት ማግኘቱ፣ ከመጽሐፍ ትርጉም ሥራ ባለፈ በርካታ ስትራቴጂካዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታዎችን የያዘ ነው።
እንደ ቻይና ዓይነት እጅግ የዳበረ የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ያላት እንዲሁም ከማኦ ዜዱንግ እስከ ዴንግ ዚያኦፒንግ፣ አሁን ደግሞ እስከ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የዘለቀ ጠንካራ የርዕዮተ ዓለም መስመር ያላት ሀገር "መደመር"ን ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ወደ ራሷ ቋንቋ መተርጎሟ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪና ትኩረት ሳቢ ፍልስፍና ማበርከት መቻሏን ያረጋግጣል።
ይህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ካፒታሊዝም እና ሶሻሊዝምን የመሳሰሉ ከውጭ የሚመጡ ርዕዮተ ዓለሞችን ብቻ ስታስተናግድ የኖረችበትን የታሪክ ምዕራፍ በመቀየር፣ አሁን የራሷን ሀገር በቀል ፍልስፍና ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ ነው።
መጽሐፉ አፍሪካን፣ መካከለኛው ምሥራቅን በዓረብኛ፣ ደቡብ እስያን በኡርዱ፣ እንዲሁም አሁን ደግሞ ምሥራቅ እስያን በቻይንኛ ቋንቋ ተደራሽ ያደርጋል፡፡
ይህም ፍልስፍናው ከተወለደበት የኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ አህጉራትን እና የተለያዩ ባህሎችን የማስተሳሰር እና የማቀራረብ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅም እንዳለው በግልጽ እንደሚያሳይ ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የ"መደመር" መጽሐፍን የቻይንኛ ትርጉም በቅርቡ ይጠብቁ!