Search

ከባህር ዛፍ ወደ እንጆሪ ምርት - የእንጦጦ ተራራ አዲሱ ስኬት

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 85

በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ ውስጥ የተፈጥሮ ጸጋን፣ ምቹ የአየር ንብረትን እና የመሬት አቀማመጥን አገናዝቦ እውቀትን መሠረት ያደረገ ልማት ማካሄድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።

ቀደም ሲል በባህር ዛፍ ደን ብቻ ይታወቅ የነበረው ታሪካዊው የእንጦጦ ተራራ፣ ዛሬ ለገበያ ከፍተኛ እሴት ያለው እና ለሥነ-ምግብ ጠቃሚ የሆነው እንጆሪ በስፋት የሚመረትበት ስፍራ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ እና የግብርና እምቅ አቅም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ "እንጦጦን ለባህር ዛፍ ነበር የምናውቀው፤ በዚህ ደረጃ እንጆሪ የሚበራከትበት እና ምግብ የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ አስበን አናውቅም፤ ነገር ግን የእንጦጦ ከፍታ ለእንጆሪ ምርት ምን ያህል ምቹ እንደሆነ በእውቀት ላይ ተመሥርቶ በመለየቱ ወደ ተግባር ሊገባ ችሏል" ብለዋል።

ይህ ስኬት ግብርናን በዘመናዊ እውቀት እና በአዲስ አስተሳሰብ መምራት ምን ያህል ውጤታማ እንደሚያደርግ ትልቅ ማሳያ ነው።

የእንጦጦን ምሳሌ ስንመለከት ቀደም ሲል የነበረውን የተለመደ አሠራር በመስበር፣ የአካባቢውን ከፍታ እና የአየር ንብረት ለምን ዓይነት ከፍተኛ እሴት ላለው ምርት እንደሚስማማ በጥናት እና በእውቀት መለየት መቻሉ ለውጡን አምጥቶታል።

"ይሄ ከፍታ እኮ ለእንጆሪ ይሆናል" የሚለው ዕይታ ወደ ተግባር ሲቀየር፣ እንጦጦ ከማገዶ እና ከባህር ዛፍ ምርት ባለፈ ውድ እና ተፈላጊ የሆኑ ፍራፍሬዎች የሚመረቱበት የምግብ መገኛ መሆን ችሏል።

ይህ የሚያሳየው የሀገራችንን ሥነ-ምኅዳራዊ ጸጋዎች በተገቢው እውቀት ካገዝናቸው የግብርና ምርታማነታችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደምንችል ነው።

የእንጆሪ ምርት መስፋፋት የገንዘብ አቅምን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ልዩ ልዩ አስተዋጽኦዎችን ያካተተ ነው።

የሀገር በቀል እውቀት ሽግግር፣ የጉልበት፣ የእንክብካቤ እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ማኅበረሰቡ ለፕሮጀክቱ ስኬት ያበረከተው ትልቅ ሀብት ነው።

ዜጎች በየደረጃው ያላቸውን ሙያ እና ጉልበት ለልማቱ ሲያውሉ፣ የልማቱ ቀጥተኛ ባለቤት እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ ተሳትፎ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሥራ ባህልን የሚያሳድግ እና ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ ነው።

የግል ባለሀብቱ በቴክኖሎጂ፣ በገበያ ትሥሥር እና በካፒታል ረገድ ያደረገው ተሳትፎ የእንጆሪ ምርቱን ወደ ዘመናዊ የንግድ መስመር እያሸጋገረው ነው።

እንጆሪ ለሆቴሎች፣ ለጭማቂ ቤቶች፣ ለኬክ ቤቶች እና ለኤክስፖርት የሚሆን ሰፊ የገበያ ፍላጎት ያለው በመሆኑ፣ የግል ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ መሰማራታቸው ሀገራችን ከፍራፍሬ ኤክስፖርት የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ መንገድ ከፍቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የተነሣው የእንጦጦ የእንጆሪ ልማት ስኬት፣ ለሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ጥሩ አርአያ የሚሆን እና ትምህርት የሚሰጥ ነው።

እውቀትን፣ የተፈጥሮ ጸጋን፣ የግል ባለሀብቱን አቅም እና የዜጎችን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በማስተናበር ረገድ የተመዘገበው ስኬት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊደገም ይገባል።

ኢትዮጵያ ያላትን የተለያየ የአየር ንብረት በአግባቡ በመጠቀም፣ በባህላዊ ሰብሎች ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኗን አቁማ እንደ እንጆሪ ባሉ ከፍተኛ እሴት ባላቸው ምርቶች ላይ በማተኮር የግብርና ልማቷን እና የዜጎቿን ሕይወት ማሻሻል ትችላለች።

በዮናስ በድሉ