Search

ከአሜሪካ እስከ ቻይና፤ የቱሪዝም ቢሊዮኖች ሚስጥር እና ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲስ ጉዞ

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 68

ቱሪዝም 21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም ኢኮኖሚ ትልልቅ አሽከርካሪዎች አንዱ እና ዋንኛው ነው። አንዳንድ ሀገራት በየዓመቱ ከቱሪዝም ብቻ በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ያገኛሉ።

ይህ ገቢ ግን በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ ለአስርተ ዓመታት የተደረገ ዕቅድ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የቅርስ ጥበቃ፣ የማስታወቂያ ሥራ እና የመዳረሻዎች ልማት ውጤት ነው።

ዛሬ የዓለም ታላላቅ የቱሪዝም ኃያላን ሀገራት ሀብታቸውን እንዴት ወደ ኢኮኖሚ ኃይል እንደቀየሩ ሲታይ፣ ኢትዮጵያም ባለፉት ስምንት ዓመታት የጀመረችው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለወደፊት ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ይታያል።

አሜሪካ፤ መዝናኛን፣ ቢዝነስን እና ፈጠራን አንድ ላይ ያስተሳሰረች ሀገር ስትሆን፣ በዓለም ከፍተኛ የቱሪዝም ገቢ ከሚያገኙ ሀገራት አንዷ ናት።

ለዚህ ስኬት ያበቃትም የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ የመዝናኛ ኢንዱስትሪዋ፣ የንግድ ጉዞዎች፣ ከተሞቿ እና የቴክኖሎጂ ልማቷ ነው።

ከኒውዮርክ እስከ ላስ ቬጋስ፣ ከግራንድ ካንየን እስከ ዲዝኒ ወርልድ፣ ለእያንዳንዱ ጎብኚ የሚመጥን መዳረሻ የፈጠረችው አሜሪካ፣ ቱሪስቶች ገንዘባቸውን በሆቴሎች፣ በመጓጓዣ፣ በግብይት ማዕከላት እና በመዝናኛ ተቋማት ላይ እንዲያወጡ የተሟላ ሥርዓትን ገንብታለች።

የአውሮፓዋ ስፔን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ታስተናግዳለች። የሜዲቴራኒያን ባሕር ዳርቻዎች፣ የታሪክ ከተሞች፣ የእግር ኳስ ባህል እና የምግብ ቱሪዝም ዋና መስህቦቿ ናቸው።

ቅርሶቿን አስጠብቃ በዘመናዊ መንገድ ለዓለም ያቀረበችው ስፔን፣ የታሪክ ሀብቷን በተራ ሕንፃ አላስቀመጠችውም፤ የኢኮኖሚ ኃይል አድርጋ ተጠቅማበታለች።

ፈረንሳይም ለረጅም ጊዜ በዓለም ከፍተኛ ጎብኝዎችን የምትቀበል ሀገር ሆና ቆይታለች። የአርት፣ የፋሽን፣ የታሪክ እና የምግብ ባህል ሀገር መሆኗ የሚሊዮኖችን ቀልብ ይስባል።

ፈረንሳይ ቅርሶቿን እንደ ሀገራዊ ማንነት ብቻ አላየቻቸውም፤ እንደ ኢኮኖሚ ሀብትም ተጠቅማባቸዋለች። በዚህም የቱሪዝም ዘርፍ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ቻይና የሺህ ዓመታት ታሪክ፣ የባህል ቅርሶች እና ዘመናዊ ከተሞች ያሏት ሀገር ናት። የቻይና ታላቁ ቅጥር፣ የተከለከለችው ከተማ፣ ዘመናዊ ሻንጋይ እና ሌሎች መዳረሻዎች በየዓመቱ ሚሊዮኖችን ይስባሉ።

ቻይና ትራንስፖርትን፣ ሆቴል ኢንዱስትሪን እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በማዘመን የቱሪስቶችን ቆይታ እና ወጪ አሳድጋለች።

ጣሊያን በታሪክ እና በአርት፣ ታይላንድ በአገልግሎት ጥራት፣ ቱርክ በባህልና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ደግሞ በዘመናዊ መስኅቦች የቱሪዝም ኃይል ሆነዋል።

እነዚህ ሁሉ ሀገራት የሚጋሩት አንድ ሚስጥር አለ። ያላቸውን ሀብት ብቻ አልያዙትም፤ ለዓለም አቀረቡት፣ አስተዋወቁት፣ አለሙት እና የገቢ ምንጭ አደረጉት።

ኢትዮጵያ ከዓለም ጥንታዊ ሥልጣኔዎች አንዷ ናት። የተፈጥሮ ሀብት፣ የባህል ብዝኃነት፣ የታሪክ ቅርሶች እና ልዩ የሆነ የሰው ልጅ ታሪክ ይዛለች። ነገር ግን ለብዙ ዓመታት ይህን እምቅ አቅም በሚገባ ወደ ኢኮኖሚ ኃይል መቀየር አልተቻለም ነበር።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ግን፣ የመደመር መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በቱሪዝም ዘርፍ ጉልህ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክቶች የዚህ ለውጥ ትልቁ ምሳሌ ናቸው። ወንጪ-ዶንዲ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ሀላላ ኬላ የመሳሰሉ መዳረሻዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር በሚችል መልኩ ተገንብተዋል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ገጽታ ለውጥ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ እና ሌሎች ዘመናዊ መዝናኛ ማዕከላት የከተማ ቱሪዝምን እያነቃቁ ነው።

ቱሪዝም የሆቴል ገቢ ብቻ አይደለም። የትራንስፖርት፣ የግብርና፣ የዕደ ጥበብ፣ የመዝናኛ እና የአገልግሎት ዘርፎችን በአንድ ጊዜ ያንቀሳቅሳል። ይህን የተረዱት ሀገራት በቱሪዝም ቢሊዮን ዶላሮችን እያገኙ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ውበቷን፣ የታሪክ ሀብቷን፣ የሃይማኖት ቅርሶቿን እና የባህል ብዝኃነቷን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር ካጣመረች በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ስፍራ የምታገኝበት ዕድል ከፍተኛ ነው።

የዓለም ታላላቅ የቱሪዝም ኃያላን ሀገራት የሚያስተምሩን ትልቁ ትምህርት አንድ ነው። ሀብት መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም፣ ሀብቱን አልምቶ ለዓለም ማቅረብ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ የማይደገም ታሪክ፣ አስደናቂ ተፈጥሮ፣ የባህል ብዝኃነት እና የሰው ልጅ ታሪክ የሚጀምርባት ምድር መሆኗን በዓለም ለማሳየት እየተንቀሳቀሰች ነው።

ዛሬ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች በቀጣይ ዓመታት በተጠናከረ ማስተዋወቅ እና በተሻለ አገልግሎት ከታጀቡ፣ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ እና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ በእጅጉ ሊጨምር ይችላል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ