በአፋር ሀዳር ተገኝታ ኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለዓለም የገለጠችው ሉሲ (ድንቅነሽ) ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ተሸኝታለች።
ሉሲ በቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ሙዚየም ለህዝብ እይታ ክፍት ሆና እንደምትጎበኝ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።
በጉዞው ሰላም የተሰኘችው ቅሪተ አካልም ለጎብኝዎች እይታ የምትቀርብ ሲሆን ሉሲም ሆነ ሰላም ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት ጉዞ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
የሁለቱ ቅሪተ አካላት ጉዞ የኢትዮጵያ ታሪክና ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ የሚደረገው አውደርዕይ ከሳይንሳዊ ሁነቱ ባሻገር የኢትዮጵያን ታሪክ ባህላዊ ሀብቶችና አስደናቂ መልክዓ ምድሮች ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
እስከዛሬ ኢትዮጵያ ሉሲን አስተዋውቃለች አሁን ደሞ ሉሲ ኢትዮጵያን እንድታስተዋውቅ ያለመ ጉዞ እንደሆነም በሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ብሔራዊ ሙዚየም ኃላፊ ዶክተር ሚካኤል ሉካሽ ሉሲና ሰላም ቅሪተ አካል በሙዚየማችን ለጉብኝት መምጣታቸው ለተቋማችን ታሪክ ትልቅ ዕድል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የፕራግ ብሔራዊ ሙዚየም በቀን እስከ 50 ሺህ ሰው እንደሚጎበኘው መረጃዎች ያሳያሉ።
ከአውሮፓውያኑ ነሀሴ 25 የሚጀምረው ዓውደርዕዩ ለ2 ወራት የሚቆይ እንደሆነ ተገልጿል።
መቅደላዊት ደረጀ