ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‘ቱሪዝም - አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ቱሪዝም የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው፤ የሀገራችንን ገጽታ በጋራ እንገንባ ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ ወይም የሚዲያ ጥረት ብቻውን በቂ አለመሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዱ ዜጋ በእኔነት ስሜት የሀገሩ አምባሳደር በመሆን የጋራ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክና ውበት ለዓለም ለማሳየት በየቦታው እየተዘዋወሩ የሚሠሩ በርካታ ወጣቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።
የዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን በቱሪዝም ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ በጥልቀት የዳሰሱት ጠቅላ ሚኒስትሩ፣ የታክሲ ሾፌሮች ቱሪስቶችን ከኤርፖርት ሲቀበሉ አላስፈላጊ የሆኑ የችግር ወሬዎችን በማውራት እንግዶችን ከማስደንገጥ ይልቅ፣ የሀገራችንን መልካም ገጽታ ሊያስተዋውቁ ይገባቸዋል ብለዋል።
በተመሳሳይ የሆቴል ባለቤቶችና ሠራተኞች ንጽህናቸውን በመጠበቅና ማራኪ መስተንግዶ በማቅረብ የእንግዶችን ልብ ሊገዙ ይገባልም ነው ያሉት።
የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎችም ቢሆኑ ድህነትን ከማሳየት ወጥተው ልክ እንደ ዓለም አቀፉ የፊልም ኢንዱስትሪ የሀገራችንን ውብና የለሙ አካባቢዎች በማሳየት የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ዳያስፖራው ሀገሩን ጠንቅቆ በማወቅ ለልጆቹ ሊያስተምርና ፖለቲካን ከሀገር ገጽታ ግንባታ ነጥሎ ኢትዮጵያን በሚገባት ክብር ሊገልጻት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ድሃ ያደረገን አለማወቅ ሳይሆን፣ አሮጌው አስተሳሰባችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዲጂታል እውቀት ያለው አዲሱ ትውልድ የነቃ አመለካከትን በመያዝ ያሉንን ጸጋዎች ወደ ሀብት ቀይሮ ሀገርን የሚጠቅምበት ጊዜ አሁን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተረባረብንና ያለመታከት ከሠራን የድካማችን ውጤት እጅግ ያማረ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።