በኢትዮጵያ በተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ የተወሰደው የቱሪዝም ዘርፍ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ትንሣኤው ተበስሯል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እንደገና አበበ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ የባህል እና ሰው ሠራሽ ጸጋዎች ያሏት ቢሆንም ቀደም ሲል ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች።
ይህንን ክፍተት ለመሙላትም በመደመር መንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ‘ገበታ ለሸገር’፣ ‘ገበታ ለሀገር’ እና ‘ገበታ ለትውልድ’ን የመሳሰሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማደስ፣ እንዲሁም አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎችን እና መሠረተ ልማቶችን የመገንባት ሥራ መከናወኑን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
እነዚህ ስትራቴጂያዊ የልማት ሥራዎች ለዘርፉ አዲስ ዕይታ መፍጠር ከመቻላቸው ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት እና ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።
መንግሥት በዘርፉ ላይ ያደረገው ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ያፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር እንደገና፣ ይህም በቱሪስት ፍሰት መጠን ብቻ ሳይሆን በጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ ጭምር እየተለካ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከለውጡ በፊት ከ5 እስከ 7 ቀናት ብቻ የነበረው የአንድ ቱሪስት አማካይ የቆይታ ጊዜ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 16 ቀናት ከፍ ማለቱን አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ድርጅት (UN Tourism) መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ የ15 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።
ቱሪዝም በባሕሪው የዓለም አቀፍ ንግድ አካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዘርፉን ይበልጥ ዘላቂ እና ተመራጭ ለማድረግ የተዘጋጀው አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ እና የተቃኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም የሀገራችንን የኢኮኖሚ ምኅዳር ይበልጥ ለማስፋት እና ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ዶክተር እንደገና አመላክተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ