ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችና የውጭ እንግዶች ከሚያስገቡት የገንዘብና የንግድ ጥቅም ባሻገር፣ አዳዲስ ዕውቀቶችንና መረጃዎችን የምንቀስምባቸው ታላላቅ ዕድሎች መሆናቸውን ‘ቱሪዝም - አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።
ለዚህም በጅማ አካባቢ ድሮ የነበረውን ዓለም አቀፍ የቡናና የጥሪኝ ንግድ እንዲሁም የንጉሥ አባ ጅፋርን አስደናቂ የአመራር ጥበብ በምሳሌነት አንስተዋል።
ንጉሥ አባ ጅፋር በሊሙና በሌሎች የታወቁ ገበያዎች ለመገበያየት ከአረብ ሀገራት የሚመጡ ዋና ዋና የውጭ ነጋዴዎችን በደረሱ ማግስት ቤተመንግሥት በመጥራት ልዩ የእራት ግብዣ ያዘጋጁላቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።
የእራቱ ግብዣ ዋነኛው ዓላማም በዚያ ዘመን ቴሌቪዥንም ሆነ መጽሔት በሌለበት ሁኔታ፣ በነጋዴዎቹ ሀገር ምን አዲስ ቴክኖሎጂ፣ ምን ዓይነት ዕውቀትና ፍላጎት እንዳለ ለመረዳትና መረጃን በውይይት ለመቅሰም እንደሆነ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን እውነት በራሳቸው የሥራ ዘመን ካጋጠማቸው ሌላ አስገራሚ ታሪክ ጋር አያይዘው በመግለጽም፣ በአንድ ወቅት የውጭ እንግዶችን ይዘው በአዋሽ ፓርክ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማበረታታት በሄዱበት ጊዜ÷ እንግዶቹ ከራሱ ከፓርኩ ሁኔታ በላይ በአካባቢው በብዛት በበቀለው የአካሲያ (ግራር) ዛፍ እጅግ መገረማቸውን አስታውሰዋል።
እንግዶቹም ከአካሲያ ዛፍ የሚቀሰመው ማር በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊና ምርጥ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ሁሉ ዛፍ እያለ በአካባቢው የንብ ቀፎ ባለመኖሩ እንደገረማቸው መናገራቸውንም አመልክተዋል።
ይህንን የውጭ እንግዶች አስተያየት መነሻ በማድረግ በጥናቱ መሠረት በተግባር ተሞክሮ ትልቅ የስኬት ፍሬ እንደተገኘበት ገልጸዋል።
ይህም ከውጭ እንግዶችና ከቱሪስቶች ጋር የምናደርገው መስተጋብር እኛ ራሳችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ያላስተዋልናቸውን የሀገራችንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአዲስ መነጽር አይተን እንድንማርና እንድንጠቀምባቸው ትልቅ ዕድል የሰጠ ነው ብለዋል።