Search

እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ የገበያ ሞሎች ሀገራችንን በአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጓታል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 53

በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ የገበያ ሞሎች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርጓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ሙሉ ለማድረግ እና የጎብኚዎችን የሽመታ ፍላጎት ለማርካት ታስበው የሚገነቡት እነዚህ ግዙፍ እና ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ የወደፊት የንግድ እና የቱሪዝም ምኅዳሩን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀይሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ማጠናቀቂያ ላይ የደረሱ አራት ግዙፍ ሞሎች በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች ልዩ የሚያደርጋቸው የተገነቡበት የሥነ ሕንፃ ጥበብ እና ጥቅም ላይ የዋሉት የቤት ውስጥ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሞሎቹ በአወቃቀራቸው፣ በኮሪደር ስፋታቸው እንዲሁም ለግንባታቸው በዋሉት የማርብል እና የፖርስሊን ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ ከሚባሉት ተርታ የሚመደቡ ናቸው።

ይህ የላቀ ጥራት የገበያ ማዕከላቱን የመግዛት እና የመሸጥ ስፍራ ብቻ ሳይሆኑ፣ የራሳቸው የሆነ ማረፊያ፣ ውበት እና ሳቢ የቤት ውስጥ የመዝናኛ ድባብ ያላቸው መዳረሻዎች ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።

ግዙፎቹ የገበያ ማዕከላት የዋና ከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀየር ባለፈ፣ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሚፈልጉትን የዓለም አቀፍ ደረጃ የሽመታ እና የመዝናኛ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማርካት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

ከዚህ ቀደም መሰል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜጋ የገበያ ማዕከላት እጥረት የነበረባት ኢትዮጵያ፣ እነዚህ አራት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ሥራ ሲጀምሩ በአንድ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ እና የተሻለ የገበያ ሞል ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደሚያሰልፏት እና ምናልባትም በአፍሪካ ቀዳሚ ሊያደርጓት እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

በበረከት ሽመልስ