Search

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ707.4 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በአንድ ዓመት አሰባሰበ

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 96

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ዓመት ውስጥ 707.4 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ታሪካዊ አፈፃፀም አስመዝግቧል።

ባንኩ በበጀት ዓመቱ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን 80 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍም አስመዝግቧል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የኢትጵያ ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ 707.4 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡን 2.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች 648 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንም ተናግረዋል።

ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ 2 ዓመት ውስጥ 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን አስረድተዋል።

ባንኩ በቀጣዩ ዓመት 832 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንዲሁም ገቢውን 360 ቢሊየን ብር ለማድረስ ማቀዱንም ተናግረዋል። 

በበጀት ዓመቱ 90 በመቶ የሚሆነውን ወይም 588 ቢሊየን ብሩን ለግል ዘርፍ ማበደሩን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ባንኩ 546 ቢሊየን ብር ብድር ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸው፣ አፈጻጸሙም ከባለፈው ዓመት አንጻር 91 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት።

ስኬቱም የባንኩ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ኃላፊነት በመውሰድ በቁርጠኝነት የሠሩት ሥራ እንዲሁም የደንበኞችና የመንግሥት ድጋፍ ውጤት መሆኑን በማንሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመቅደስ እንዳለ