Search

የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም፡ ስጋቶችን አስቀድሞ የመቀልበስ ብቃት እና ብሔራዊ ተቋማዊ ቀጣይነት

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 59

 

የኢትዮጵያ የጸጥታ መዋቅር ላለፉት ጥቂት ዓመታት ያከናወናቸው መጠነ ሰፊ ሪፎርሞች የአገራችንን የውስጥ ፖለቲካዊ መረጋጋት ብቻ ሳይሆን፣ የቀጠናውን የኃይል ሚዛን ጭምር የቀየሩ ተለዋዋጭ ክስተቶች ሆነዋል።

ይህ የሪፎርም ጉዞ ቀደም ሲል ሥር ሰደው በነበሩት ተቋማዊ ድክመቶች፣ በፓርቲ እና በብሔር ጥገኝነት፣ እንዲሁም ዘመኑን ባልዋጁ የአደረጃጀት ዘይቤዎች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነበር።

የሀገራችን ዋናው ትኩረት የጸጥታ ተቋማቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት በታማኝነት እንዲያስጠብቁ ማስቻል ነው፡፡

ይህ ደግሞ በተግባር የሀገራችንን የመከላከል አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። በተለይም በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ግንባታ እና በስትራቴጂካዊ ዕቅድ ረገድ የተከናወኑት ሥራዎች የጸጥታ መዋቅሩን ይበልጥ ተወዳዳሪ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርገውታል።

በዚህ የሪፎርም ሂደት ውስጥ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያደረገው ዘመናዊነትን የማስፈን ሥራ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

ሠራዊቱ ከተለመደው የእግር ጉዞ እና ባሕላዊ የውጊያ ስልት ወጥቶ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትጥቅ መደራጀቱ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የኃይል ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ ቀይሮታል።

ዘመናዊ ድሮኖች፣ የተራቀቁ የሳይበር መከላከያ ስልቶች እና የመረጃና ደኅንነት መዋቅሩ መዘመን የጸጥታ ተቋማቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የውስጥና የውጭ ስጋቶችን አስቀድመው የመከላከል አቅማቸውን አሳድጎላቸዋል።

 

ከዚህ በተጨማሪም የባሕር ኃይል በድጋሚ መደራጀቱ እና የአየር ኃይልን የመታጠቅ እና የመዋጋት አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር፣ ኢትዮጵያ በሪፎርሙ አማካኝነት የቀጠናውን ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድር የመቆጣጠርና የመምራት አቅሟን ማሳደጓን በግልጽ ያሳያል።

ሪፎርሙ የጸጥታ መዋቅሩን የመከላከያ አቅም ከማሳደግ ባለፈ በኢትዮጵያ ቀጠናዊ ዲፕሎማሲ እና የውስጥ ልማት ደኅንነት ላይ የጎላ ሚና እንዲጫወት አስችሎታል።

ጠንካራ እና አስተማማኝ የጸጥታ መዋቅር መገንባቱ ሀገራችን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክቶቿን ያለምንም የውጭ ስጋት እንድትጠብቅ እና እንድታጠናቅቅ ትልቅ አቅም ሆኗል።

ይህ ተቋማዊ ጥንካሬ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላት የዲፕሎማሲያዊ ሚና ከፍ እንዲል ያደረገ ሲሆን፣ የማንኛውንም የውጭ ኃይላት ስትራቴጂካዊ ጫናዎች የመቋቋም አቅም ፈጥሯል።

 

የጸጥታ መዋቅሩ አሁን ላይ የደረሰበት ቁመና የሀገርን ህልውና አስተማማኝ ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያን ቀጠናዊ ተሰሚነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የሪፎርሙ ሌላኛው ስኬት በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ የጸጥታ ስጋቶችን የመቆጣጠር እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅም ላይ የታየው ተራማጅ ለውጥ ነው።

ከፌዴራል ፖሊስ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ድረስ ያሉ ተቋማት ለዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ቴክኖሎጂዎችን እና የተደራጁ የሰው ኃይሎችን በመገንባታቸው የሕዝብን ሰላም የማረጋገጥ አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።

የጸጥታ ተቋማቱ ገለልተኝነት እና ብቃት በተለይም ሀገራዊ ማሻሻያዎችን እና የልማት እንቅስቃሴዎችን ያለምንም መስተጓጎል ለማስቀጠል ወሳኝ መሠረት ሆኗል።

አዲሱ አደረጃጀት በሕዝብ እና በጸጥታ አካላት መካከል የነበረውን የጥርጣሬ ግንኙነት ወደ መተማመን እና አጋርነት በመለወጥ ረገድም አመርቂ ውጤት እያሳየ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሪፎርም በዋናነት የተመሠረተው የወደፊት ስጋቶችን አስቀድሞ በመተንበይ እና ዝግጁነትን በማሳደግ ላይ በመሆኑ ተቋማዊ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ ሆኗል።

አሁን ባለው የዓለም አቀፍ እና የቀጠናዊ ፖለቲካ ተለዋዋጭነት ውስጥ ጠንካራ የጦር ኃይል እና ዘመናዊ የደኅንነት መዋቅር መያዝ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ኢትዮጵያ በተግባር አሳይታለች።

ሪፎርሙ የሀገራችን መከላከያ ይበልጥ ዘመናዊ፣ ተንቀሳቃሽና በማንኛውም ምኅዳር ላይ ተልዕኮውን በብቃት መወጣት የሚችል አድርጎታል።

ይህም አገራችን በቀጠናው ሰላም ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ተጨማሪ ኃይል ከመሆኑም በላይ፣ በስትራቴጂካዊው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማንም በቀላሉ የማይጋፋትና የማይበገር የኃይል ሚዛን ማዕከል አድርጓታል።

ይህ የተቋማት መልሶ ግንባታ ሂደት የሰው ኃይል ጥራትን በማሳደግ ረገድም ሰፊ ርቀት ተጉዟል።

የመከላከያ እና የደኅንነት አካላት ምልመላ እና ሥልጠና ከቀደሙት የፖለቲካና የዝምድ እና አሠራሮች ተላቆ ሙሉ በሙሉ በችሎታ፣ በዕውቀት እና በብቃት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ተደርጓል።

በተለይም በከፍተኛ የጦር ትምህርት ቤቶች እና አካዳሚዎች የሚሰጡ ሥልጠናዎች የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁና የዘመኑን የጂኦፖለቲካ ስሌቶች የሚረዱ ስትራቴጂስቶችን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ ተሻሽለዋል።

ይህ በዕውቀት የተገነባ የሰው ኃይል በጦር ሜዳም ሆነ በደኅንነት ረገድ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ የበላይነት እንድትቀዳጅ አስችሏታል።

ከተቋማዊ ማሻሻያዎቹ ጎን ለጎን፣ የጸጥታ መዋቅሩ ከኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ደኅንነት ጋር ያለው ቁርኝትም በከፍተኛ ሁኔታ ጎልብቷል።

በተለይም ሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት እያደረገችባቸው ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የትራንስፖርት ኮሪደሮችንና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ከማንኛውም የጥፋት ኃይሎች ጥቃት የመጠበቅ ብቃቱ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

ይህም የውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት በማሳደግ ረገድ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር ማለት የኢኮኖሚ ዕድገትና የፖለቲካ መረጋጋት ዋስትና መሆኑን በተግባር ያሳየው ይህ ሪፎርም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ስትራቴጂካዊ መሪነቷን እንድታረጋግጥ አድርጓታል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ መዋቅር አሁን ላይ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለዓመታት የተካሄደው ጥልቅና ስልታዊ የሪፎርም ሥራ ውጤት ነው።

ተቋማቱ ከፖለቲካዊና ብሔር ተኮር አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ ነፃ በመሆን የሀገርን እና የሕዝብን የጋራ ደኅንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገውታል።

ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ የሚደቀኑባትን ፈተናዎች በራሷ አቅም የመመከት ብቃቷን ያረጋገጠበት ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል።

ወደፊትም ይህንን ተቋማዊ ጥንካሬ ይበልጥ በማጠናከር የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግና የሰው ኃይልን ማብቃት የአገርን ዘላቂ ሰላምና ቀጠናዊ ተሰሚነት ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኙ መሣሪያ ሆኖ ይቀጥላል።

በበረከት ሽመልስ