የሀገራችን ብልጽግና መሠረቱ ከገጠሩ ማኅበረሰብ ኑሮ መሻሻልና ከኢኮኖሚ ጥንካሬ ጋር የተቆራኘ ነው።
የገጠሩን ማኅበረሰብ ክብር፣ ምቾት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመረው ጉዞ በሀማሳ ምድር ሌላ ታሪካዊና ህያው ፍሬ አፍርቷል።
የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውና በ79.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ዘመናዊው የሀማሳ ሞዴል መንደር በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ይህ ሞዴል መንደር የመኖሪያ ስፍራ ብቻ ሳይሆን፣ የአርሶ አደሮችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ጥራትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ዘመናዊ ሥነ-ምህዳር የተገነባበት ነው።
በመንደሩ ውስጥ የተሟሉላቸው ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለንጹህ ኃይል አማራጭ የሚሆኑ የባዮ ጋዝ መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ምቾትና ጤና ተስማሚ የሆኑ የመኖሪያ መንደሮች የገጠሩን ህይወት ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየሩ የልማት ማሳያዎች ናቸው።
ከአኗኗር ዘይቤ መዘመን ባሻገር፣ መንደሩ አርሶ አደሩን በምጣኔ-ሀብት ራሱን እንዲችልና ገቢውን እንዲያሳድግ ታስቦ የተገነባ ነው።
ለእንስሳት እርባታ የሚሆኑ ዘመናዊ ማደሪያዎች፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የጓሮ አትክልት ስፍራዎች እና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የንብ ቀፎዎች በስፋት የተካተቱበት በመሆኑ ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ብልጽግናን እንዲጎናጸፉ ያደርጋል።
ይህም አርሶ አደሩ ከተለምዷዊ አሠራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊና ስኬታማ የግብርና ባለቤትነት እንዲሸጋገር በር ይከፍታል።
የሀማሳ ሞዴል መንደር መመረቅ የኢትዮጵያ ገጠር እምቅ አቅም በተግባር ወደ ልማት እየተቀየረ መሆኑን የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ ክብሩንና ምቾቱን የጠበቀ ዘመናዊ የአኗኗር ስልት መፍጠር እንደሚቻል ያሳየን ይኸው ሥራ፣ ወደ ሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም በስፋት በመስፋፋት የኢኮኖሚ ልዕልናችንን የሚያፋጥን ይሆናል።
በሔዋን ጌታቸው