Search

የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የኢትዮጵያን የተስፋ ጉዞ የሚወስን ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው - ምሁራን

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 42

 የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የኢትዮጵያን የተስፋ ጉዞ የሚወስን ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉ አንጋፋ ምሁራን ገለጹ።

ዜጎች ለምክክሩ ስኬታማነት እስካሁን ያሳዩትን የነቃ ተሳትፎ ማጠናክር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዋናው ሀገራዊ ምክክሩ የሚቀርቡ የተለያዩ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ይፋ አድርጓል።

እነኚህም ዋና ዋና የጉባኤው አጀንዳዎችም የሀገር ግንባታ፤ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፤ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ጉዳይ፤ የሃይማኖት ጉዳዮች፤ የተቋማት ግንባታ፤ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፤ ሙስናና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ናቸው።

የሀገራዊ ምክክሩ የእስካሁኑ ጉዞ፤ እውነተኛ አሳታፊነትን፣ ፍፁም ግልጽነትን እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማካተት ሥራዎችን በስኬት በማከናወን ላይ ይገኛል።

የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮች የሚፈቱበት አማራጭ የሌለው ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ከሚያራርቃቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸው እንደሚበልጡ ነው የጠቆሙት።

ይህም ምክክሩ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ በመመካከር እና በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።

ይህ ሂደት ኢትዮጵያን በተሟላ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና ምክክሮቹም ወደ ሀገራዊ መግባባት የሚወስዱ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን የተጓዘበት ሂደት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የሕዝብ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አኳያ የተመዘገበው ስኬት በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪ እና የሕግ ጠበቃው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም፣ የሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እየተቀየረ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት እንዳይግባቡ ያደረጓቸውን መሠረታዊ ችግሮች ራሳቸው መፍትሔ እንዲያስቀምጡላቸው በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ሥር የሰደዱ ችግሮችን በጥልቀት መመካከር አስተማማኝ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት ሁነኛ መንገድ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለምክክሩ መሳካት ወጣቶች እና ምሁራን እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በባለቤትነትና በሃላፊነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።