በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
"የወጣቶች ተሳትፎና ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው ውይይት ወጣቶች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በባለቤትነት ስሜት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ እና ለምክክሩ ውጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ግንዛቤዎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።
በተጨማሪም ምክክርን ባህል በማድረግ በየጊዜው ሊፈጠሩ የሚችሉ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ ነው።
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድህን፥ ምክክር አለመግባባቶች እና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ያለውን ሚና አብራርተዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባከናወናቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ሂደቶች ሁሉ የወጣቶች ተሳትፎና ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል።
ወጣቶች ግጭቶችን ከማባባስ ይልቅ ሰላምን በመስበክ ለሀገሪቱ ሰላም መረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ገልፀዋል።
በዚህም እንደ ሀገር ሲንከባለሉ የቆዩ ቁርሾዎች በምክክር እንዲፈቱ እየተደረገ ላለው ጥረት ውጤታማነት ወጣቶች በባለቤትነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ
#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ሀገራዊምክክር #የወጣቶችተሳትፎ