Search

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ በጋምቤላ

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 101

በጋምቤላ ክልል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር  የተተከሉ ችግኞችን በማህበረሰቡ ተሳትፎ የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ የላሬ ወረዳ ነዋሪዎች በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም በተደረገላቸው ድጋፍ በማህበር ተደራጅተው በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኛንቲክ ቱት እና ኛቦት ኑድ ከአሁን ቀደም  በአካባቢያቸው ያልተለመዱ የፍራፍሬ እና የቀርከሀ ችግኞችን ተንከባክበው በማሳደግ  ተጠቃሚ ለመሆን በጋራ በመሥራት ላይ  ነን ብለዋል።

በጋምቤላ ክልል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙላት ቢረጋ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከ35 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የደን እና የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።

ማህበረሰቡን በተፋሰስ ልማትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ አደራጅቶ በማሳተፍ ከአረንጓዴ ዐሻራ የኢኮኖሚ ተጠቀሚነትን ለማሻሻል እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል፥ በተያዘው ዓመት በክልሉ በተካሄደው ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር የማህበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች በችግኝ ተከላው ያሳዩትን የነቃ ተሳትፎ በእንክብካቤ ሥራውም አጠናክረው  መቀጠል  እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ጋምቤላ #አረንጓዴዐሻራ