የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው፥ አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ 63 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልፀው፤ ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ48 በመቶ ዕድገት እንዳለው አክለዋል።
የገጠር ቀበሌዎችን እና መንደሮችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ፥ ከዋናው ግሪድ 140 ቀበሌዎችን እና መንደሮችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 148 የሚሆኑትን ተጠቃሚ በማድረግ ከ100 ፐርሰንት በላይ መፈፀም መቻሉን ተናግረዋል።
የኃይል ብክነት ችግርን በመፍታት ረገድ አገልግሎቱ ነባር ቆጣሪዎችን በዘመናዊ ስማርት ቆጣሪዎች የመተካት ስትራቴጂ ነድፎ እና ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ሥራ በመግባት እስከ በበጀት ዓመቱ ማብቂያ 53 ሺህ 714 ስማርት ቆጣሪዎችን ወደ አገልግሎት ማስገባቱን ጠቅሰዋል።
የስድስቱ ከተሞች (ሻሸመኔ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ) የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አፈፃፀም በአሁኑ ወቅት 99.4 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ኤሌክትሪክ የተገናኘላቸውን ጨምሮ የአገልግሎቱ ደንበኞች ቁጥር 5.21 ሚሊዮን መሻገሩን አንስተው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም 800 ሺህ አዲስ ደንበኞችን ለማፍራት መታቀዱን ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት እና የዲስትሪቢዩሽን መሠረተ ልማት እርጅናን ጨምሮ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልፀዋል።
በትዕግስቱ ቡቼ
#EBC #EBCdotstream #EEU #performance