የመደመር እሳቤ በሚዛናዊ የእሳቤ ውቅር የተቃኘ ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሥርዓት ግንባታ ማሳለጫ ነው። ታሪክና ቅርስን ከአዲስ ዕይታ ጋር በማቀናጀት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መዋቅራዊና ስትራቴጂያዊ ለውጥ አምጥቷል።
የመደመር እሳቤ አካታች፣ አስተሳሳሪና አሰባሳቢ የእሳቤ ማዕቀፍ በመሆን በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አዲስ አቅጣጫ የቀየሰ እሳቤ ነው። ይህ እሳቤ «እኔና እኔ ብቻ» ከሚል ቁንፅል ዕይታ በመውጣት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴቶችን በማጠናከር፣ ኃይልን በማስባሰብና በጋራ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ ነዉ።
ይህ የፉክክርና የትብብር ሚዛን መጠበቅ ለጋራ ብልጽግና በጋራ የመትጋት ቅኝትን የሚያበረታታ ሲሆን፣ ልዩነቶችን ያከበረ ሙሉዕ ዕይታ በመፍጠር ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መሰረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህ በሚዛናዊነት ላይ የተገነባው የመደመር እሳቤ በተለይም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፋች እየሆነም ይገኛል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በአብዛኛው በሰሜኑ ታሪካዊ መስመሮች ማለትም በአክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና በደቡብ ባህላዊ መስመር ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም የመደመር እሳቤ ግን ይህንን ዕይታ በከፍተኛ ደረጃ ቀይሮታል።
በዚህም መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞች ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ተደርጓል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የተገነቡት የሸገር፣ የእንጦጦ፣ የወዳጅነት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየምና የዓድዋ መታሰቢያ ፕሮጀክቶች መዲናዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ከመሆን ባለፈ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ተመራጭ መዳረሻ አድርገዋታል።
ከዚህ በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነትና መሪነት በቀረቡት "ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ሀገራዊ ጥሪዎች አማካኝነት እንደ ኮይሻ፣ ሃላላ ኬላ፣ ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ሌሎች ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎች ወደ ግዙፍ የቱሪስት መስህብነት ተቀይረዋል።
የመደመር እሳቤ ዋነኛ ምሰሶ ቅንጅት በመሆኑ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተሳስረው እንዲለሙ ተደርጓል። ወደ አዳዲሶቹ የቱሪስት ማዕከላት የሚወስዱ ዘመናዊ መንገዶች፣ የቴሌኮም አውታሮችና የኤሌክትሪክ አቅርቦቶች አብረው የተገነቡ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ በረራዎችን ከአዳዲሶቹ መዳረሻዎች ጋር የማቀናጀት ስራ በስፋት ተከናውኗል።
በሌላ በኩል ዕሳቤው "ሀገርን ማወቅ" እና "የራስን ማድነቅ" በሚሉ እሴቶች ላይ በመመስረት የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲነቃቃ ትልቅ መነሳሳት መፍጠሩ ተመላክቷል።
ይህም ኢትዮጵያውያን በዓላትንና የዕረፍት ጊዜያትን በሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዲያሳልፉ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት የቱሪዝም ዘርፉ ሙሉ በሙሉ እንዳይጎዳ እንደ ትልቅ ደጋፊ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል።
የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልማትና በዘመናዊ ስልጣኔ ላይ ወደተገነባ አዎንታዊ ገጽታ ለመቀየር ቱሪዝምን እንደ ዋነኛ መሣሪያ ተጠቅሞበታል። ታዋቂ የዓለም መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት እንደ አንድነት ፓርክ ያሉ አዳዲስ መስህቦችን እንዲጎበኙ በማድረግ ውጤታማ የገጽታ ግንባታ ስራ ተከናውኗል።
በተጨማሪም የዘርፉ ልማት አካታችነትን ባረጋገጠ መልኩ በአዳዲሶቹ መዳረሻዎች ዙሪያ የሚኖሩ የአካባቢው ማህበረሰቦች በቅርሶች ጥበቃ፣ በግብርና አቅርቦት እና በእደ ጥበብ ሥራዎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን የግሉ ዘርፍ በሆቴል፣ በሎጅና በቱር ኦፕሬተርነት በስፋት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
በአጠቃላይ በመደመር እሳቤ ስር የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከተገደበ ባህላዊ ዕይታ ወጥቶ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ፣ የከተሞች ውበት መገለጫ፣ የሀገር ገጽታ መገንቢያ እና የማህበረሰብ የሥራ እድል ፈጣሪ እንዲሆን ስትራቴጂያዊ ለውጥ የተደረገበት ሲሆን ይህም ትልቋ ኢትዮጵያ በሚመጥናት የትልቅነት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: