በዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር ውስጥም የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ልክ እንደዚሁ ከፍተኛ ጥንቃቄን፣ አስተዋይነትንና ረቂቅ ጥበብን የሚጠይቅ ፈታኝ ጉዞ ነው።
በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆች መሠረት የአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም በአግድም እና በቁመት እርከኖች ይከፈላል።
በጎንዮሽ ሲታይ የሕልውና፣ ከፍተኛ፣ ዋና እና አነስተኛ ተብሎ ሲመደብ፤ በከፍታ ደግሞ የሀገር ደህንነትና ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ጥቅም፣ ምቹ የዓለም አቀፍ ሥርዓት መፍጠር እንዲሁም የራስን እሴትና ባህል ማስፋፋት በሚሉ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ይዋቀራል።
በዚህ ውስብስብ የጥቅም ትስስር ውስጥ የሀገር ደህንነት፣ የሕልውና እና የግዛት አንድነት ጉዳዮች በፍጹም ድርድር የማይደረግባቸው ቀይ መስመሮች ናቸው።
የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በተወሰነ ደረጃ መደራደር ቢቻልም፣ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ግን ለድርድር አይቀርብም።
በሌላ በኩል የምዕራባውያኑ ዓለም የራሱን እሴት በፊልም፣ በሙዚቃ እና በሥነ-ጽሑፍ በማስፋፋት የሌላውን ዓለም ትውልድ ሲያማልል፤ የአፍሪካ ሀገራት ግን አሁንም ከመሠረታዊ የእለት ጉርስ ልመና ባለመውጣታቸው ይህ የባህልና እሴት ማስፋፋት ጉዳይ ለእነሱ ቅንጦት ሆኖ ይታያል።
ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ "የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ምንድነው?" የሚለው ጥያቄ በግንባር ቀደምትነት ይነሳል።
የፖለቲካ ትንታኔዎች እንደሚያሳዩት ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና እና እጅግ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
ጥያቄው የሀገር ደህንነትና የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑ በግልጽ ከተለየ በኋላ፤ ቀጣዩና ወሳኙ ምዕራፍ ይህንን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ብሔራዊ ጥቅም በምን መንገድ እናሳካዋለን የሚለው ነው።
ይህንን የሕልውና ግብ ከዳር ለማድረስ በዲፕሎማሲ፣ በጥበብ እና በተለየ ስልት መንቀሳቀስ የግድ ይላል። በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት እና የስትራቴጂ አውጪዎች እጅግ የጠራ ጥበብና ማስተዋል ሊኖራቸው ይገባል።
ታሪካዊ ጠላቶች ወዳጅ መስለው፣ መሬቱን አረንጓዴ ሣር አልብሰው፣ ከስሩ ግን መውጫ የሌለው የጥፋት ገደል ቆፍረው ሊጠብቁ ስለሚችሉ፤ የሀገርን አንገብጋቢ ጥቅም ለማስከበር የሚደረገው ጉዞ በጥልቀት የታሰበበት፣ ስሜታዊነትን ያስወገደ እና ከስውር የጂኦ-ፖለቲካ ወጥመዶች የነቃ ሆኖ እየተሰራበት ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: