ጦርነትና ግጭት መቼም ቢሆን ዘላቂ መፍትሔ አምጥተው አያውቁም፤ እውነተኛው ድልና ፈውስ የሚገኘው መሣሪያን አስቀምጦ በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት መቀመጥ ሲቻል ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ የነገ ዕጣ-ፈንታም የተንጠለጠለው በዚህ የሰለጠነ የውይይትና የይቅርታ መንገድ ላይ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከአርማ ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያውያን የጦር መሣሪያዎቻቸውን አስቀምጠው ወደ መመካከር ሲመጡ ካለፉ ስህተቶቻቸው መማር እንደሚጀምሩ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ረጅም እና ኩሩ ታሪክ ያህል፣ በሂደቱ የተፈጠሩ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ስብራቶች ጥለውት ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
እነዚህን የቆዩ ጠባሳዎች ለማከም ታሪክን ለበቀል ወይም ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እንደማይገባ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ያለፉ ስህተቶችን በግልጽ አምኖ በመቀበልና ይቅርታን በማስቀደም የጋራ መግባባት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ታሪካዊ ትረካዎች ሀገርን የሚያፈርሱ መሣሪያዎች ከመሆን ይልቅ፣ ለነገ የምንማርባቸው መስተዋቶች እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻለው በብስለትና በሰለጠነ መንገድ በሚደረግ አሳታፊ ምክክር ብቻ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሀገራዊ ምክክሩ ከማህበረሰቡ ርቀውና ተገልለው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመልሰው ከወገናቸው ጋር ተቀላቅለው መኖር እንዲችሉ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርና ይህም ወደ ፍትህ ለመምጣት ወሳኝ መንገድ እንደሚሆን ፕሮፌሰር መስፍን ያላቸውን ተስፋ አጋርተዋል።
ይህ ሂደት የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋን የኢትዮጵያ ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን እጅግ ወሳኝ፣ ጥልቅ የሆነ ብሔራዊ ራዕይን ያነገበ፣ ሀገርን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና ያለፉ ቁስሎችን በጥበብ ለማከም አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ስኬታማ ሆኗል ተብሎ የሚታመነው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፣ የወረዳ ተወካዮች በትክክል በእኩልነት ተሰሚ ሆነው፣ ሀሳባቸውን በነጻነት ገልጸውና ተደምጠው፣ እርስ በእርስ ተከባብረው በተወሰኑ አጀንዳዎች ላይ ብቻ እንኳን መግባባት ላይ መድረስ ከቻሉ ትልቅ ድል መሆኑን አብራርተዋል።
መግባባት ያልተቻለባቸውን አጀንዳዎች ደግሞ ቦታ አሲዘው ለቀጣይ ስራ ኃላፊነት በመስጠት የመጨረሻው ጉባኤ ላይ መድረስ ከተቻለ፣ ለኮሚሽኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ በቆይታቸው አስረድተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: