Search

በአዲስ አበባ የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከ97 በመቶ በላይ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ተሸጋገሩ

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 252

በ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 97.48 በመቶ የሚሆኑት 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የፈተና ውጤቱን ይፋ ለማድረግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ ፈተናውን ከወሰዱ 84 ሺህ 257 ተማሪዎች መካከል 82 ሺህ 137 የሚሆኑት ውጤታማ መሆን ችለዋል።

ይህ የዘንድሮው አፈጻጸም በ2017 ዓ.ም ከነበረው የ95 በመቶ የማለፍ ምጣኔ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ እድገት ያሳየ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ውጤቱ እንዲመዘገብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ መምህራን፣ የትምህርት አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ወላጆችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ዘንድሮ ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ሥራው ልዩ ትኩረት መስጠቱ፣ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠናክሮ መቀጠሉ እንዲሁም የሂሳብ እና እንግሊዘኛ ትምህርት ስትራቴጂ ተነድፎ በትኩረት መሠራቱ በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶ/ር ዘላለም አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመማሪያና ማስተማሪያ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው እና ከወላጆች ጋር በቅንጅት መሠራት መቻሉ ለስኬቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገልጿል።

በከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ሥርዓቱ የብዝሃ ቋንቋ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የተማሩ ተማሪዎች በትምህርት ዓይነቶቹ ፈተና መውሰዳቸውን ኃላፊው አስታውሰዋል።

የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ካስፈተኑ 768 ትምህርት ቤቶች መካከልም 543 ያህሉ ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳለፋቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል።

ተፈታኝ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ የተዘጋጀውን ይፋዊ የኢንተርኔት ሊንክ በመጠቀም ውጤታቸውን መመልከት የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: