Search

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ 10.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡- ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 135

ኢትዮጵያ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 10.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሏን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር  ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ባከናወናቸው ተግባራት በሀገራችን የንግድ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ማስመዝገቡን ነው  ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ያስተወቁት።

ተቋሙ በዲጂታላይዜሽን ሽግግር፣ በደንበኞች አገልግሎት እና በውጭ ንግድ ገቢ ረገድ አዳዲስ ክብረወሰኖችን ሰብሯል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ከሀገራዊ የወጪ ምርቶች 9.40 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት 10.80 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል። ይህም ከዕቅዱ በላይ ገቢ በማግኘት ከፍተኛ ውጤት መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ዘንድሮ በውጭ ንገድ የተገኘው ገቢ ካበለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.5 ቢሊዮን ዶላር (30.12%) አስደናቂ ጭማሪ የታየበት መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።

ተቋሙ ያለምንም ተጨማሪ የውጭ ኢንቨስትመንት ወጪ፣ በውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ባለሙያዎች አቅም ብቻ በርካታ የዲጂታል አገልግሎቶችን በሥራ ላይ በማዋል የዲጂታል አሰራርን በማስፋፋት ረገድም አርዓያ የሚሆን ስራ ሰርቷል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ 3.3 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማገልገል ታቅዶ፣ ዕቅዱን በማሳለጥ 3.4 ሚሊዮን እና ከዚያ በላይ ደንበኞችን ማገልገል ተችሏል።

ለሀገር ውስጥና ለውጭ ንግድ ትልቅ ፋይዳ ያለው የኢ-ኮሜርስ (e-commerce) የግብይት ሥርዓት ዝግጅት ተጠናቅቆ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ በይፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንና የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚዛንን መሰረት ያደረጉ በርካታ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል ተብሏል።

በሚኒስቴሩ በተከናወኑ ተግባራት በብዙ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ምርቶች እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ምርቶች ጥራታቸው ተረጋግጦ ለንግዱ ማህበረሰብ እንዲቀርቡ መደረጉን ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

በብሩክታዊት አስራት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: