Search

ኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርትና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉራችንን የነገ ተስፋ ለመቅረጽ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 208

ኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርት እና በዲጂታል ፈጠራ የአፍሪካን የነገ ተስፋ ለመቅረጽ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባች እየተካሄደ የሚገኘውን የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት «MedEDAfrica 2026» አህጉራዊ ጉባኤን ዛሬ በይፋ ከፍተዋል።

በዚሁ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የአፍሪካ የነገ ጤና እና ተስፋ የሚወሰነው ዛሬ በሚዘጋጀው ወጣት የሕክምና ኃይል ላይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለዚህ አህጉራዊ ግብ መሳካት ተግባራዊ ቁርጠኝነቷን እያሳየች ትገኛለች ብለዋል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ባለሙያዎችን ትምህርት ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መፍሰሱንና በመላ በኢትዮጵያ የሕክምና ትምህርትን ለማዳረስ ያልተማከለ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ሀገራችን ከራሷ ፍላጎት ባለፈ ከአፍሪካ ሀገራት የመጡ የጤና ባለሙያዎችን በከፍተኛ የሕክምና ትምህርት ተቋሞቿ በማስተማር እንደ ቀጣናዊ የልቀት ማዕከል እያገለገለች መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

አያይዘውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ፈጠራ የአህጉሪቱ መሪ ለመሆን ራሷን እያዘጋጀች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምርምር ውጤቶችም የፖሊሲ መመሪያ በመሆን የሕዝቡን ሕይወት በተግባር ሊለውጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአህጉሪቱ በጋራ ማስተማር፣ በጋራ ፈጠራን ማምጣት እና በጋራ መምራት ከተቻለ እውቀት ሰብዓዊነትን የሚያገለግልባትን ጤናማ አፍሪካን መገንባት እንደሚቻልም በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: