በ”ኸርት አታክ ኢትዮጵያ" አስተባባሪነት ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጣው ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን በአዲስ አበባ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማካሄድ አረንጓዴ አሻራውን አኖረ።
ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከሩዋንዳ፣ ከሕንድና ከሌሎችም ሀገራት የመጡት እነዚህ ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ይፋዊ የሕክምና አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ባካሄዱት በዚህ መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ሥራው በሰዎች ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃ ላይም ዘላቂ ተጽዕኖ የመፍጠር ዓላማ አለው።
የቡድኑ አስተባባሪዎች ኢትዮጵያ እስካሁን ወደ 48 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን መትከሏን መረዳታቸውን ጠቁመው፣ ባለፈው የሕክምና ዘመቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም የዚህ ታላቅ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ አጋርተዋል።
ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት ችግኝ መትከልን ከልጅ አስተዳደግ ጋር በማነጻጸር፣ ልጆችን ተንከባክበን ለታላቅ ቁምነገር እንደምናበቃቸው ሁሉ እነዚህም ችግኞች አድገው አስደናቂ ዛፎች እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ይህ መርሃ ግብር ሰዎችን በሕክምና ከመደገፍ ባለፈ ለወደፊቱ ትውልድ የምናበረክተው ትልቅ ስጦታ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህ ሰብዓዊነት ለተሞላው ተግባራቸውም በጠቅላይ ሚኒስትሩና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ልባዊ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የዲቦራ ፋውንዴሽን መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳም የሕክምና ቡድኑ አባላት እያበረከቱ ስላለው ሁለንተናዊ የሕክምና ድጋፍና ስላኖሩት አሻራ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ የልብ ቀዶ ጥገና ቡድን በኢትዮጵያ በሚኖረው የሁለት ሳምንታት ቆይታ፣ በተፈጥሮ የልብ ሕመም እና በሩማቲክ የልብ ሕመም ለሚሰቃዩ በርካታ ሕፃናትና አዋቂዎች ነጻ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ይሰጣል።
የሕክምና ዘመቻው ለብዙ ሕሙማንና ለቤተሰቦቻቸው ታላቅ እፎይታንና አዲስ የሕይወት ተስፋን እንደሚፈነጥቅ ይጠበቃል።
መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው "ኸርት አታክ ኢትዮጵያ" በሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን የሕክምና ባለሙያዎች የተመሠረተ በሕግ ዕውቅና ያገኘ ለትርፍ ያልቆመ ተቋም ነው።
ድርጅቱ በኢትዮጵያና ውሎ አድሮም በመላው አፍሪካ በልብ ድካምና በስትሮክ ሳቢያ የሚከሰተውን ያለዕድሜ የመቀጨት አደጋ ለመግታት፣ የልብና የደም ዝውውር ሥርዓት ሕክምናን በማስፋፋት ዘላቂ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: