Search

ታላቁን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለመጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች ተጠናቅቀዋል፡- ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ሰኞ ሰኔ 29, 2018 159
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ የሆነውን ታላቁን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለመጀመር የሚያስችሉትን የዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የቅድመ ዝግጅት መርሐ ግብሮች የሚጀምረው ይህ ጉባኤ፣ ይፋዊና ዋና የምክክር ስብሰባዎቹን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ማካሄድ ይጀምራል።
በመድረኩ ላይ ከየክልሎቹ፣ ከየክፍለ ከተማው እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎችን ደህንነትና ምቹነት ለመጠበቅ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ለአካል ጉዳተኞች እና ለአቅመ ደካሞች ልዩ ድጋፍ የሚሰጡ አሰራሮች የተመቻቹ ሲሆን፣ ህጻናት ልጆች ያሏቸው ሴት ተሳታፊዎች በምክክሩ ላይ በተረጋጋ መንፈስ መሳተፍ እንዲችሉ በባለሙያ የሚመሩ የህጻናት ማቆያ ስፍራዎች ተደራጅተዋል ተብሏል።
ከተሳታፊዎች ጋር አብረው የሚንቀሳቀሱ እና ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ፍላጎታቸውን ተረድተው የቅርብ እገዛ የሚያደርጉ በርካታ በጎ ፈቃደኞች ከኮሚሽኑ ባለሙያዎች ጋር ስለመመደባቸወም ነው የተገለፀው፡፡
ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አኳያ የየብስ፣ የባቡር እና የአየር ትራንስፖርት አማራጮች ዝግጁ ተደርገዋል፤ የጸጥታና ደህንነት ሁኔታን በተመለከተም ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ የጥበቃ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብሏል ኮሚሽኑ።
በተጨማሪም በማዕከሉና በማደሪያ ቦታዎች ጊዜያዊ የሕክምና ማዕከላት የተደራጁ ሲሆን፣ ድንገተኛ አደጋዎችን ጨምሮ የላቀ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ተሳታፊዎች ሆስፒታሎችና አምቡላንሶች ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ ዳር መሀል ሳይል ከ1 ሺህ 300 በላይ ወረዳዎች ድረስ በመድረስ የአርሶ አደሮች፣ የአርብቶ አደሮችና የሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመስማት በርካታ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ማሰባሰቡን ገልፆ ሁሉም ተሳታፊዎች እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ በመግባት ለኮሚሽኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል።
በመሐመድ አልቃድር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: