Search

የሲኖትራክ ተሸከርካሪ የጥራት ጉድለት ሳይሻሻል ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ታግዷል - የጉምሩክ ኮሚሽን

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 143

የሲኖትራክ ተሽከርካሪ ያለበትን የጥራት እና የቴክኒክ ችግር እስኪያሻሽል ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መታገዱን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል።

የጥራት ጉድለቱ በየጊዜው የሰው ሕይወት ብሎም ንብረት እንዲጠፋ ምክንያት በመሆኑ፤ አምራች ድርጅቱ ማሻሻያ እስከሚያደርግ ድረስ ተሸከርካሪው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መከልከሉን ነው የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዘሪሁን አሰፋ ለኢቢሲ ዶትስትሪም የተናገሩት።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ላይ ባለው የጥራት እና የቴክኒክ ጉድለት ምክንያት በሰው ሕይወት ላይ በየጊዜው አደጋ እያደረሰ መሆኑን በመጥቀስ ለጉምሩክ ኮሚሽን ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በላከው ደብዳቤ መጠየቁን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክሩ ገልፀዋል።

ተሽከርካሪውን የሚያመርተው ኩባንያ በምርቶቹ ላይ ማስተካከያ እስከሚያደርግ ድረስ ከግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ክልከላው ተግባራዊ መደረጉንም ገልፀዋል።

በዚህም ከተጠቀሰው ዕለት ጀምሮ ምንም ዓይነት የማስገቢያ ፈቃድ እንዳልተሰጠ አረጋግጠዋል።

በአፎምያ ክበበው

#ebcdotstream #customs #SinoTruck #ban