ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ያቀረቡት ሀገራዊ የሰላምና የአብሮነት ጥሪ፣ "የመደመር መንግሥት" ፍልስፍናን በተጨባጭ መሬት ላይ ያወረደ ሥነ-ምግባራዊና ፖለቲካዊ መግለጫ ነው።
ልክ በለውጡ ወደ ስልጣን ሲመጡ እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም ያ የአብረን እንስራ ጥሪ እንዳልደበዘዘ በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡
አዲሱ መንግሥት ዛሬም እንደትናንቱ አብሮ ለመስራት ቂምን ለመሻገር ፣በፍቅር ለመተሳሰር ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት በአደባባይ አሳይቷል፡፡ ይህም የዕሳቤው መነሻ ገና ከጅምሩ የመደመር መንግሥት እሳቤ መሆኑና ከትናንት እስከዛሬ ያልታጠፈው የሰላም ጥሪ መሰረቱ ይኸው መደመር መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የመደመር ዋነኛ ማዕዘን አቃፊነትን መከተልና ሁሉንም አይነት ሀሳብና ዜጋ ማሳተፍ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪም ይህንኑ ሚዛን ጠባቂነትና አሰባሳቢነት በጉልህ የሚያንጸባርቅ ነው።
ከጽንፎች መላቀቅና ሀገራዊ ጸጋዎችን ማሰባሰብ የመደመር ትልቁ መገለጫ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "ጽንፈኝነት አንፈልግም፣ ባንዳነት አንፈልግም፣ ዘረኝነት አንፈልግም" በማለት መግለጻቸው፣ የመደመር ፍልስፍና ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ከሚያስወግደው፣ እንዲሁም ከዜሮ ድምር ጨዋታ ወጥቶ በአንድነት ከመትመም መርሁ ጋር ፍጹም የተገመደ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ የጋራ ሀገሩን ማጽናትና ማበልጸግ እንደሚመኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ይህም በመደመር እሳቤ መሰረት የሁላችንም አበርክቶ አስፈላጊ መሆኑንና "ሁላችንም እናስፈልጋለን" የሚለውን መርህ በተግባር የሚያሳይ ነው።
የመደመር መንግሥት መደፍጠጥን ፈጽሞ የማይቀበልና አቅፎ በሚዛን መጓዝን የሚመርጥ ስርአት ነው። ይህንንም በተግባር ለማሳየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ተፎካካሪዎችን አካቶ ኢትዮጵያን ማልማት እንደሚፈልግ፣ ኢትዮጵያ የጋራ ሀገር መሆኗንና በምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዘርፍ ተባብረን ሀገርን እንድናበለጽግ ሰፊ ጥሪ አቅርበዋል።
"ሰላም ነው የሚያስፈልገን፣ ትብብር ነው የሚያስፈልገን ፣ አብረን መስራት ነው የሚያስፈልገን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ላሉ ታጣቂ ኃይሎች የሰላም በራቸው ክፍት መሆኑን በማረጋገጥ ለእርቅ ያላቸውን የጠለቀ ቦታ አሳይተዋል።
በመደመር መንግሥት እሳቤ ውስጥ መፈራረስና መጠፋፋትን ሳይሆን መገንባትንና አብሮነትን መምረጥ የህልውና መሰረት ነው። በዚህም መሰረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በተቻለ መጠን በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ለመፍታት፣ በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎች እና በጫካ ያሉ ሰዎች በይቅርታ ለማስገባት፣ ለመተው ልባችን ሰፊ መሆን ይኖርበታል" በማለት ጥልቅ የሆነ የይቅርታ ልብን ለሀገር ግንባታ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የአካታች ሀገራዊ ምክክሩም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በነጻነት የሚወያዩበት መድረክ መፈጠሩ የዚሁ አሰባሳቢነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ አካሄድ የመደመርን "ተጓዳኝነትና የሕይወት አንድነት" (Syntropy) እሳቤን ይወክላል። በቀውስ መሀል ፈውስን፣ በመፈራረስ ውስጥ መታደስን፣ ተበታትኖ በመጥፋት መካከል ተሰባስቦና ተጣምሮ በአዲስ ጉልበት መነሳት የመደመር ትክክለኛ መንገድ ነው።
ይህ "አብረን እንደግ" የሚል የሰላም ጥሪ፣ በመደመር ሥነ-ምህዳር ውስጥ "ህልውናዊ አብሮነትና ተደጋጋፊነት" (Symbiosis) እና "የጋራ ጥረትና የኃይል ብዜት" መደመር በመባል ከሚታወቁት እሳቤዎች ጋር ይገናኛል።
ሕይወት ከራሳችን እኩል በሌሎች ነዋሪነትና ቀጣይነት ላይ የተመሰረተች በመሆኗ፣ አብሮ ማደግ የፈጣን ዕድገት በር መሆኑን የመደመር መንግስት ያምናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት "እንሰብሰብ፣ 1 እንሁን፣ እንከባበር፣ በሰላም እንነጋገር፣ አብረን እንደግ፣ በተሰራው ስራ እንኩራራ፣ አዳዲስ ድል እናምጣ" የሚለው ሀሳብ በሙሉ የመደመር እሳቤ መገለጫ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ የሃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በመጠቀም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገራዊ ሰላምና ብልጽግና በጋራ እንዲቆም የሚያደርግ ነው። ይህ ከጽንፍ የተላቀቀ አካታችነት፣ ሚዛን ጠባቂነትና አሰባሳቢነት፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በይቅርታና በአብሮነት ላይ ለመገንባት የተነደፈውን የመደመር መንግስትን የጠለቀ ርዕይ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: