የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የክልሉን የግብርና ፖሊሲ እና የአርሶ አደሮችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማበልፀግና በማላመድ አበረታች ውጤቶች እያስመዘገበ ይገኛል።
የዚሁ ስኬት አካል የሆነውና በወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የማህበረሰብ አሳታፊ የበጎች አውራ መረጣና ሥርጭት የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ፣ ኢንስቲትዩቱ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በማጎልበት እንዲሁም ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኛ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ ግብርና እንዲስፋፋ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም 69 ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና 210 የምርምር አጀንዳዎችን በማዘጋጀት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
አክለውም የማህበረሰብ አቀፍ የዝርያ ማሻሻያ ሥራው የበጎች ዘረመል በማሻሻል፣ ምርጥ አውራዎችን በማሰራጨት የአርቢዎችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን ገቢ ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ገልጸው፣ የመስክ በዓሉም በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮዎችን ለመቀመርና ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚረዳ ግብዓት የሚሰበሰብበት መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቀድራላ ዋበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በማዕከሉ የግብርና ምርት እድገት ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችሉ ከ195 በላይ የምርምር ሥራዎች ተሰርተው ቴክኖሎጂዎችን የማስረጽ ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ ነው።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የበግ ዝርያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የዶዮገና የበጎች ምርምር ዘርፍና የጉመር የምርምር ዘርፍ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በዳልጋ ከብቶች፣ በአነስተኛ አመንዣኪ እንስሳት፣ በዶሮ ዝርያዎችና በመኖ ማሻሻል ላይ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ በበኩላቸው፣ በዞኑ ካሉት ጸጋዎች የእንስሳት ዘርፍ ቀዳሚ መሆኑን በመጥቀስ የዝርያ ማሻሻል ሥራውን ከእንስሳት መኖና ጤና ጋር አቀናጅቶ በመስራት ውጤታማ መሆን መቻሉን ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: