የ1929 እና የ1959 የዓባይ ውኃ ስምምነቶች የላይኛውን የናይል ተፋሰስ ሀገራት ያላካተቱ በመሆናቸው በእነዚህ ሀገራት ላይ አስገዳጅ የሕግ መሠረት ሊሆኑ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ ገልጸዋል።
የ1929 ስምምነት በግብጽ እና በብሪታንያ፣ እንዲሁም የ1959 ስምምነት በግብጽ እና በሱዳን መካከል የተደረጉ ሲሆን፣ የናይል ተፋሰስን የሚጋሩ ሌሎች ሀገራት የስምምነቶቹ ተዋዋይ ወገኖች አልነበሩም።
በመሆኑም ስምምነቶቹ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ያካተተ አጠቃላይ የውኃ አስተዳደር ሥርዓት እንዳልዘረጉ ከኢቲቪ እንግሊዝኛ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
“አንድ ሀገር ተዋዋይ ወገን ባልሆነበት ስምምነት ሊገደድ አይችልም” የሚለው መርሕ በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ የዓባይ ውኃ በአንድ ወይም በሁለት ሀገራት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በበርካታ ሀገራት የሚጋራ የጋራ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ፕሮፌሰር ያቆብ አስረድተዋል።
በተፋሰሱ የላይኛው ክፍል የሚገኙ ሀገራት ለዓባይ ውኃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም በውኃው ላይ "ብቸኛ መብት አለን" የሚል ጥያቄ እንደማያነሱ ጠቅሰው፣ የውኃ ሀብቱ በሁሉም ተፋሰስ ሀገራት ትብብር መልማት እንዳለበት አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለዓባይ ውኃ ከፍተኛውን ድርሻ የምታበረክት በመሆኗ፣ የተፋሰሱ ሀገራት የውኃ ሀብታቸውን በጋራ ለማልማት እና ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ለመጠቀም የትብብር መንገድ መከተል እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የዚህ የውኃ ሀብት ልማት እና የተፋሰሱ ሀገራት ግንኙነት ዋነኛ ማሳያ ነው።
በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅሙ ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኘው ይህ ግድብ በራሷ ግዛት ውስጥ የተገነባ በመሆኑ፣ የውኃ ሀብቷን ማልማት ከሉዓላዊነቷ ጋር የተያያዘ ተፈጥሯዊ መብት መሆኑ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ አሞላል እና አሠራር ላይ ለዓመታት ድርድር ማድረጋቸውን ያወሱት ፕሮፌሰር ያቆብ፤ ኢትዮጵያ የሀገራቱን ሉዓላዊነት የሚያከብር የጋራ ተጠቀሚነት መርሕን እንደምትከተል አስገንዝበዋል።
የግድቡ አሞላል በዝናብ ወቅት በሚገኘው የውኃ ትርፍ ላይ የተመሠረተ እንደነበረ እና በአሁኑ ወቅትም ውኃው በተርባይኖች በኩል አልፎ ኃይል እያመነጨ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡
በውኃ ፍሰት ላይ የሚነሱ ክርክሮች በተጨባጭ መረጃ እና በሳይንሳዊ ጥናት መመራት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።
የዓባይ ጉዳይ በታሪካዊ ስምምነቶች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ባሳተፈ የጋራ ውይይት፣ ትብብር እና በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆች ላይ በተመሠረተ አቀራረብ መመራት እንዳለበት ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: