Search

ብሪክስ ፀረ-ምዕራባውያን ስብስብ ሳይሆን አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ነው - ተመራማሪዎች

ሓሙስ መስከረም 07, 2019 53

የኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባል መሆን በዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ከፍ ከማድረጉ ባሻገር፣ በአዳጊ ሀገራት መካከል ያለውን የጋራ ድምፅ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የፖለቲካ እና የውጭ ጉዳይ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ተመራማሪዎቹ ከኤፍኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት የብሪክስ ስብስብ ፀረ-ምዕራባውያን ጎራ ሳይሆን፣ ከባህላዊው አሠራር የተለየ ሁለገብ የትብብር ማዕቀፍ ነው።

ስብስቡ በደቡቡ ዓለም የሚገኙ ሀገራትን የጋራ ዕድገት የሚያፋጥን እና ባለብዙ ወገን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥርዓትን የሚያጠናክር ነው።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዮት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ሚፍታህ መሐመድ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የዚህ ጥምረት አባል መሆኗ ከምዕራባውያን አጋሮቿ እንዲሁም እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ሳይጎዳ ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር ሚዛኑን ጠብቃ እንድታስኬድ ያስችላታል።

ከዚህ ዲፕሎማሲያዊ ሚዛን ባሻገር አባልነቱ ብሪክስ ካቋቋመው አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት ሰፊ በር የሚከፍት ነው።

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አሊ ሁሴን (/) በበኩላቸው ይህ ዕድል የኢኮኖሚ ትስስርን በማስፋት የልማት ግቦችን ለማሳካት እና ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በውይይቱ ወቅት በዋናነት ከተነሱት ነጥቦች መካከል የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎች ይገኙበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ተመራማሪ እና የዩኒቨርሲቲ መምህር አብርሃም በርታ (/) እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በምታከናውነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዓለም ሞዴል ለመሆን እየሠራች ትገኛለች።

ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑት ተግባራት ለብሪክስ አባል ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው።

አባል ጥምረቶቹ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጥረት ትልቅ ትኩረት እና ዕውቅና መስጠታቸውን የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮችን በምታዘጋጅበት እና በምትሳተፍበት ወቅት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በአካል ተመልክቶ የሚማርበት ሰፊ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የብሪክስ አባልነት በታዳሽ ኃይል ልማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በቀጣናው ፍትሐዊ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር መንገድ የሚከፍት መሆኑ በቆይታው ተብራርቷል።

ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከማሳደጉም በላይ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ አቅሟን በአዲስ መልክ የሚገነባ ስትራቴጂካዊ እርምጃ እንደሆነ ተመልክቷል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: